ኮሚሽኑ ለአማራ ክልል ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ለአማራ ክልል ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ
ባህር ዳር ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአማራ ክልል ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የኮሚሽኑን ድጋፍ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ተረክበዋል።
የቢሮ ኃላፊዋ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግርም በክረምቱ ''አንድ ደርዘን ለአንድ ተማሪ'' በሚል መሪ ሃሳብ የትምህርት ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው አሁንም ይሄው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ላደረገው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የድጋፍ ማሰባሰቡ ዓላማም በክልሉ ማንኛውም ተማሪ በቁሳቁስ ችግር ከትምህርት ገበታ እንዳይርቅ ለማስቻል መሆኑን ተናግረው የሁላችንም ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኮምቤ፤ ኮሚሽኑ የልማት ስራዎችን ከማከናወን ባሻገር በማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ መሆኑን አንስተው ይህንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዛሬው እለትም በአማራ ክልል ለተማሪዎች ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የደብተርና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ መሰል በጎ ተግባራትን በማከናወን ማህበራዊ ሃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።