ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ለሚካሄደው የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ስኬት የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ይጠበቃል

ባሕርዳር ፤ መስከረም 26/2018 (ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልል  በቅርቡ የሚካሄደውን  የፖሊዮ መከላከያ  ክትባት ዘመቻ  ለማሳካት ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።   

በክልሉ ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም የሚካሄደውን የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንዳመለከቱት፤ የክትባት ዘመቻው ሕጻናትን ከዘላቂ የአካል ጉዳትና ሞት በመታደግ ጤናማና አምራች ትውልድ ለመገንባት የተመቻቸ ነው።


 

በዚህም ከመስከረም 30/ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ከሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

ክትባቱ የሚሰጠውም በማዕከላዊና ደቡብ ጎንደር፣ በሰሜንና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች እንዲሁም በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በደብረ ታቦርና በደብረ ማርቆስ ከተሞች መሆኑን ተናግረዋል።

የክትባት ዘመቻው ቤት ለቤት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሕፃናት መዋያዎችና ሌሎች አካባቢዎች እንደሚካሄድ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለማሳካትም በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የተቀናጀ ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል። 


 

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ቤተክርስቲያን የባህር ዳር ሀገረ ስብከት የማሕበራት ማደራጃ ክፍል ኃላፊ ሊቀ ጉባኤ  ሙሉጌታ ሐበሻ፤ ለክትባት ዘመቻው ስኬታማነት  እንደ ቤተ ክርስቲያን ከማስተማር ጀምሮ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች  ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሀመድ ሁሴን በበኩላቸው፤  ወላጆች ሕጻናት በወቅቱ እንዲያስከትቡ በማስተባበር እንደሚደግፉም ተናግረዋል።

በመድረኩ  ላይ  የክልሉ ጤና ቢሮ፣ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አመራሮች፣  የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም