ቀጥታ፡

ተማሪዎች ከመደበኛ የመማር ማስተማር ጎን ለጎን የሀገራቸውን የመስህብ ሃብቶች እንዲያውቁ ይሰራል - ቱሪዝም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡-ተማሪዎች ከመደበኛ የመማር ማስተማር ጎን ለጎን የሀገራቸውን የመስህብ ሃብቶች አውቀው እንዲያሳውቁ እንደሚሰራ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽንና በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ትብብር ''ቱሪዝምና ዘላቂ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።


 

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ46ኛ በኢትዮጵያ ለ38ኛ ጊዜ በሚከበረው በቱሪዝም ቀን የቀረበው አውደ ርዕይም ተማሪዎች ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የሀገራቸውን ቅርሶች አውቀው እንዲያሳውቁ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ አለማየሁ ጌታቸው፤ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች መከበረ መጀመሩን ገልጸዋል።

ከመዲናዋ አራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ የሀገርህን እወቅ ክበብ አባላት ተማሪዎችም ለዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ እንዲጎበኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

አውደ ርዕዩም ተማሪዎች የሀገራቸውን ታሪክና ቅርስ እንዲሁም የተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽና የባህል ሃብቶች አውቀው እንዲያሳውቁ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። 

በቀጣይም ተማሪዎች የሀገራቸውን ዕምቅ የመስህብ አቅም ተገንዝበው ለሌሎች እንዲያሳውቁ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ባለሙያ በላይ በለጠ፤ ተማሪዎችን በየትምህርት ቤቱ ዘርፈ ብዙ ዕውቀት የሚያገኙባቸውን ክበባት በማደራጀት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንን አስመልክቶ የተዘጋጀው አውደ ርዕይም ተማሪዎች የሀገራቸውን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሰው ሰራሽ የንድፈ ሃሳብ የመስህብ ሃብቶች በተግባር የሚገነዘቡበት መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የተንቀሳቃሽ አውደ ርዕዩ የጎበኙ ተማሪዎች፤ ቱሪዝም ሚኒስቴር በአለም ቅርስነት የተመዘገቡትንና ያልተመዘገቡትን ሃብቶች በማስመልከት የሰጣቸው ስልጠና ትልቅ አቅም እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

በዚህም ባገኙት እውቀት መሰረት ለሃገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ዜጎች ሃገራቸውን በሚገባ ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም