ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ደረጃቸውን የጠበቁ ቅድመ መደበኛና የሌሎች የመደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ይስፋፋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡-መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ደረጃቸውን የጠበቁ ቅድመ መደበኛና የሌሎች የመደበኛ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ እንደሚያስፋፋ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ አስታወቁ፡፡

ስድስተኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ- ሥርዓት ተካሄዷል።

በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፤ መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ደረጃቸውን የጠበቁ ቅድመ መደበኛና የሌሎች የመደበኛ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ እንደሚያስፋፋ አስታውቀዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት ክህሎት ያላቸውና ውጤታማ ባለሙያዎችን እንዲያፈሩ በሚያስችል መልኩ ይቃኛሉ ብለዋል፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ነጻነታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ፣ የአስተዳደርና የሰው ሃይል ልማታቸው የተሻሻለ እንዲሆን እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በአርብቶ አደር አካባቢ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በልዩ ሁኔታ የተቀረጸ ዕቅድ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ የቅድመ አንደኛና አንደኛ ደረጃ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

መንግስት የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግና ለማሻሻል እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም