ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዋቅራዊ ኢኮኖሚ ሽግግርን በአጭር ጊዜ የሚያሳልጥ ወሳኝ እርምጃ ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መዋቅራዊ ኢኮኖሚ ሽግግርን በአጭር ጊዜ የሚያሳልጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ። 

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የሥራ ዘመን የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የ2018 ዓ.ም የመንግስት ዋና ዋና የልማት ዕቅዶችን አቅርበዋል።

በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ባደረጉት ንግግርም፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ብቻ አይደለም ብለዋል።

ይልቁንስ የሀገራችን የፖለቲካ  ኢኮኖሚና የማህበራዊ ህይወትን የሚቀይር ወሳኝ የሽግግር ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስፋት፣ የመረጃ ልውውጥን በማቀላጠፍና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን በአጭር ጊዜ እውን የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።

በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመትም ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል አገልግሎቶች በዲጂታል ማዕቀፍ የሚሰጡበትን ምኅዳር የማሳለጥ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የዲጂታል ዘርፍ ለሌሎች ዘርፎች አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራበትም አስገንዝበዋል።

በ2025 የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ አመርቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተመዘገበውን ውጤት ለማሸጋገር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የዲጂታል ትግበራውም ለህብረተሰቡ የቀረበና እንግልትን የሚቀንስ አገልግሎት በመዘርጋት በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም ተስፋፍቶ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። 

የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ሥርዓትን በላቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማዘመን በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ አፈፃጸም በማጎልበት የመረጃ ሉዓላዊነት አቅም እንደሚገነባ አንስተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም