ቀጥታ፡

መንግስት ሁሉንም የሰላም አማራጮችን በመከተል አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እየሰራ ይገኛል -  ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡-መንግስት ሁሉንም የሰላም አማራጮች በመከተል አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን እየሰራ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡ 

ስድስተኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ- ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የተጀመረውን የሀገር የማንሰራራት ጉዞ በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት መንግስት በ2018 ዓ.ም በርካታ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ከሥርዓት መለዋወጥ ጋር የማይናዱ ነጻ፣ ገለልተኛና ህዝባዊ ብሔራዊ ተቋማትን ለመፍጠር መንግስት ጽኑ መሠረት በመጣል ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመትም አንድነታችንን እና ሰላማችንን በማይናወጥ ደረጃ ላይ ለማድረስ መንግስት በተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ ይሰራልም ብለዋል፡፡

ብሔራዊ የጸጥታ እና የደህንነት ተቋሞች የሥርዓት ለውጥን የሚሻገሩ እና የሀገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ብርቱ ተቋማት እንዲሆኑ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በሃይል ማረቅ ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ የመንግስት ጽኑ እምነት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የእርቅና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በየጊዜው የሚስተዋሉ የኃይል እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም የመንግስት ሙሉ ዝግጁነትና ዘመናዊ አቅም እንዳለው አመልክተው፤  ዛሬን በብልሃትና ትዕግስት ለነገ ዘላቂ ሰላም የሚበጅ አካሄድን መምረጡን ተናግረዋል፡፡

ይህ ቁርጠኝነት ሀገራዊ መግባባትን ለመትከል ዘላቂና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመመስረት ያለው ፋይዳ የላቀ ነው ብለዋል፡፡

ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት መላው ህዝብ እንዲሁም ልሂቃን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውንም አቅርበዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም