ቀጥታ፡

መንግስት በማህበራዊ ዘርፍ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡-መንግስት በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም በጤና፣ ትምህርትና ስፖርት ላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አስታወቁ፡፡ 

ስድስተኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ- ሥርዓት ተካሄዷል።

በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መንግስት ባለፈው ዓመት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት መስራቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በመቅረጽና በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ የትምህርት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡

መንግስት በጤናው ዘርፍ በከፍተኛ ትኩረት በሚሰራበት በሽታን የመከላከል ተግባር ውጤት መገኘቱን ገልጸው፤ አሁን ላይ አክሞ ማዳን ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የህክምና መሳሪያዎችንና መድሃኒቶችን በአገር ውስጥ ማምረት በመቻሉ  ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት አካታችነትን መሰረት በማድረግ ባከናወናቸው ተግባራት ህጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች አረጋውያንንና የአገር ባለውለታዎችን ያማከሉ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሴቶችና ወጣቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት ውሳኔ ሰጪነታቸው እንዲጨምር ተደርጓል ብለዋል፡፡

ተጋላጭ ሴቶችን በየነገዋ የሴቶች ማገገሚያና የክህሎት ማዕከል በመግባት ስልጠና በመስጠት ተሳትፏቸው እንዲጨምር መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የወጣቶችን ክህሎት በማጎልበት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የስራ ዕድሎች ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ነው ያመለከቱት።

የወጣቶችን አእምሯዊና አካላዊ ዕድገት ለማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በስፋት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ከተሰጡት በርካታ ድጋፎች መካከል ዘመናዊ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል ፡፡ 

መንግስት በተለይም በህጻናት ዕድገትና ትምህርት ላይ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ  የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም