ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፍትሕዊ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ቅቡልነት አግኝቷል - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ዘላቂነትና ፍትሕዊ የባሕር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘቱን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስታወቁ። 

የኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ምርጫም ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ተላሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ማሸጋገር እንደተቻለም ገልጸዋል።

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ÷  የኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነት ማዕከልና መሠረታዊ ማጠንጠኛው ብሔራዊ ጥቅምና የዜጎች ክብር ነው ብለዋል።

በዚህ መነሻነትም የኢትዮጵያ የጂኦ-ስትራቴጂያዊ ቁመና በመደርጀት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ምርጫም ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ተላሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ማሸጋገር ማስቻሉን አብራርተዋል።

በድንበር ተሻጋሪ ሃብቶቿም ፍትሕዊ ተጠቃሚነትን በዚያው ልኬትም አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት መብቷን ማረጋገጥ እንደሚኖርባት አጽንኦት ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ የህልውና መሠረት በሆኑት ሁለቱም ታላላቅ የውሃ ሃብቶች ዙሪያም መንግስት ያልተቋረጠ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

እስካሁን በተደረጉ ጥረቶችም ሶስት ጉልህ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ÷ በመጀመሪያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ አጋጥመውት የነበሩ ፈተናዎችን በጥበብ በማለፍ ማጠናቀቅና በደመቀ ሥነ-ስርዓት ማስመረቅ እንደተቻለ አስታውሰዋል። 

በሁለተኛነትም የኢትዮጵያ አስተማማኝና ዘላቂነት የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ከፍ ወዳለ ደረጃ የተሸጋገረበትና ፍትሕዊ ጥያቄውም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘቱን ተናግረዋል።

በሶስተኛ ደረጃም በውጭ ሀገራት ለእንግልትና ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን በክብር ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵዊያንም በሀገራቸው የልማት ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉበትን ምህዳር በመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም