የእርቅና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየተሠራ ነው - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የእርቅና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየተሠራ ነው - ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፡- መንግሥት የእርቅና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሠራ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዚዳንት ታዬ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛው የሥራ ዘመን የ2018 የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የ2018 የመንግስት ዋና ዋና የዕቅድ አቅጣጫዎች ላይ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በኃይል ማረቅና ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም፤ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ መንግሥት ጽኑ እምነት አለው ብለዋል።
የሰላም ጉዳይ እስካሁንም ሲሠራበት መቆየቱንና በያዝነው በጀት ዓመትም የመንግሥት ትኩረት ሆኖ እንደሚቀጥል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት የእርቅና የሰላም አማራጮችን በመከተል የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ መንግሥት እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ምንም እንኳን በየጊዜው የሚስተዋሉ የኃይል እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግሥት ሙሉ ዝግጁነት እና ዘመናዊ ዐቅም ቢኖረውም፤ የዛሬውን ግጭት በማሸነፍ ለነገው ትውልድ ቂምና ቁርሾ አናወርስም የሚል መርኅ በመከተል በዛሬ ብልሃትና ትዕግስት ለነገ ዘላቂ ሰላም የሚበጅ አካሄድን መርጧል ብለዋል።
ይህ እምነት ሀገራዊ መግባባትን ለመትከል፣ ዘላቂና ቅቡልነት ያለው ሀገረ-መንግሥት ለመመሥረት ያለው ፋይዳ የላቀ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት መላው ሕዝብ እንዲሁም ልሂቃን የበኩላቸውን እንዲወጡም ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል።