ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-ጂንካ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-ጂንካ ዩኒቨርሲቲ
ጂንካ፤መስከረም 26/2018 (ኢዜአ)፡- ጂንካ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው ከኣሪ እና ከደቡብ ኦሞ ዞን ከተወጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት አፈፃጸምና የቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ምክክር እያደረገ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ይትባረክ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ተልዕኮው ባሻገር በአሪ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች ባለፉት አመታት 268 የሚሆኑ ችግር ፈቺ የጥናትና የምርምር ስራዎችን አከናውኗል።
ከጥናትና ምርምር ስራዎች ባሻገር ከ 77 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 115 የተቀናጁ የማህበረሰብ ልማት ፕሮጀክቶችም መተግበራቸውን ጠቅሰዋል።
በዞኖቹ የሚካሄዱ ችግር ፈች የጥናትና ምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ሰሙ ይታፈሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ በእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሰብል ምርታማነት ማሻሻል፣ በተቀናጀ የመስኖ ልማት ላይ ዘርፈብዙ ፕሮጀክቶችን በመተግበር የአርሶና የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አከባቢው ዕምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ያሉበት በመሆኑ የቱሪዝም ሀብቶችን በሳይንሳዊ የጥናትና ምርምሮች ማሳደግ፣የመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዘመናዊ እውቀት መሰረት የሆኑ ሀገር በቀል ዕውቀቶችም እንዲጎለብቱና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል ።
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የሆኑ ሳይንሳዊ የምርምር ስራዎችን በመስራት ማህበረሰቡን እየጠቀመ መሆኑን ተናግረዋል ።
ዩኒቨርሲቲው ከማህበረሰብ አገልግሎቱ ባሻገር በአከባቢው የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በትምህርት ቤቶችም የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም በማሳደግና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑንም አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ የዞኑ አስተዳደር ከዩኒቨርሲቲው ጋር የትብብር ማዕቀፉን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።
በምክክር መድረኩ ከአሪና ከደቡብ ኦሞ ዞን የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ፣የሀይማኖት አባቶች፣የማህበረሰብ ተወካዮችና በየደረጃው ያሉ የመንግስት አመራር አባላት ተገኝተዋል ።