ቀጥታ፡

የመንግስትን ንብረት ከብክነት ለመታደግ የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ጋምቤላ፤መስከረም 26/2018(ኢዜአ)፦የጋምቤላ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የመንግስትን ገንዘብና ንብረት ከብክነት ለመታደግ የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የኦዲት ግኝቶችን በማስመለስ ረገድ የነበሩ ውስንነቶችን ለማረም አዲስ ደንብና መመሪያ ማዘጋጅቱንም ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

‎የመስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ኦዲተር ሉል ቦል ለኢዜአ እንደገለጹት መስሪያ ቤቱ የመንግስትን ገንዘብና ንብረት ከብክነትና ከምዝበራ ለመከላከል የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እየሰራ ነው።

‎በተለይም የኦዲት ዓይነትና ተደራሽነቱን በማስፋት የመንግስት በጀትና ንብረት በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል በማድረግ ረገድ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

‎ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ባለፈው በጀት ዓመት ባካሄደው የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ከ147 ሚሊዮን ብር በላይ የሰነድ ክምችት፣ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እንዲሁም ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ወጪዎችን ማግኘቱን ለአብነት አንስተዋል።

‎በዘንድሮው በጀት ዓመትም በ82 የክልል፣ የዞንና የወረዳ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የፋይናስ፣ የክዋኔና የአካባቢ ኦዲት ስራዎችን ለመከወን እቅድ ይዞ ወደ ትግበራ መግባቱን ተናግረዋል።

‎እቅዱን ስኬታማ ለማድረግም የተቋሙን የሰው ኃይል አደረጃጀት በማሻሻልና አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

‎ከዚህም በተጨማሪ የኦዲት ግኝቶችን በማስመለስና በማስተካከል ሂደት የነበሩ ከፍቶችን ለመሙላት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ከምክር ቤቱ የኦዲት ፎረም ጋር በመቀናጀት የእርምት እርምጃ  ለመውስድ የሚያስችል ደንብና መመሪያ ማዘጋጀቱንም አቶ ሉል ገልጸዋል።  


 

‎የክልሉ ምክር ቤት ፕላን፣ በጀት፣ ፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኡቦንግ ኡቶው እንዳሉት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ከዓመት ወደ ዓመት በኦዲት ግኝትና በሽፋን ረገድ የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገበ ነው።

‎ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በደንብና መመሪያ ክፍተት ምክንያት የኦዲት ግኝቶችን በማስመለስና በማስተካከል በኩል ውስንነቶች የነበሩበት መሆኑን ተናግረዋል።

‎አሁን ላይ ቀደም ሲል በኦዲት ግኝት ማስመልስ ሂደት የነበሩ ውስንነቶችን ለመሙላት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ከምክር ቤቱ ፎረም ጋር በመቀናጀት ክፍተቱን የሚሞላ ደንብና መመሪያ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም