ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ዕቅድ ፕሮጀክቶች ለኢንዱስትሪ ዕድገት መፋጠን ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል-የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤መስከረም 26/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ዕቅድ ፕሮጀክቶች ለኢንዱስትሪ ዕድገት መፋጠን ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4/2017 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ወቅት የ30 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማብሰራቸው ይታወቃል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግና የዳንጎቴ ግሩፕ የዩሪያ ማዳበሪያና በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የሚገነባውን የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

በመቀጠልም በሶማሌ ክልል በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ጋዝ ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ ለምርቃት በቅቷል።

የተመረቀው የኦጋዴን የመጀመሪያ ዙር ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ ፋብሪካ እና የግንባታ መሠረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ፕሮጀክቶችም ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጣቸው ናቸው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለኢንዱስትሪ ምርታማነት የተደረገው ድጋፍ ዘርፉ ተጨባጭ ዕድገት እንዲያስመዘግብ መሰረት ጥሏል ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተመርቀው ለአገልግሎት የበቁና የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችም ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ትርጉም እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

በተለይም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ እና የተፈጥሮ ጋዝ የማዕድን ልማት ፋብሪካ ፕሮጀክቶች የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ተጨማሪ የኢንዱስትሪ ግብዓት በመሆን ለኢኮኖሚ ማንሰራራት መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ፕሮጀክቱም የአርሶ አደሮችን የግብዓት አቅርቦት ፍላጎት በማሟላት የግብርና ምርታማነትን ለማስቀጠል ጭምር የማይተካ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።

የተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካ ፕሮጀክቱም አምራች ኢንዱስትሪው አማራጭ የኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ በማስቻል የምርት ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለኢንቨስትመንት ፍሰት ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በመጀመሪያ ዙር የተመረቀው የተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካም የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዕድገት ተመጋጋቢነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትጵያን ሀገራዊ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠልም በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ምርታማነት ለማነቃቃት የተወሰዱ ሀገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የፖሊሲ እርምጃዎችም ለዘርፉ ዕድገት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም