በሀገራዊ ምክክሩ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክሩ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ተዘጋጅተናል
ሐረር፤ መስከረም 26/2018 (ኢዜአ)፡- በሀገራዊ ምክክሩ የነቃ ተሳትፎ በማድረግና ይህንን ታሪካዊ እድል በመጠቀም ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ተዘጋጅተናል ሲሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን "የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ሚና እና አስተዋጽኦ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሀሳብ የውይይት መድረክ በሐረር ከተማ አካሂዷል።
ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ ከሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር የተውጣጡ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳትፈዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ወይዘሮ ረውዳ መሀመድ እና ወጣት ሙባረክ ዩሱፍ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ በንቃት በመሳተፍ ስለ ሀገር ጉዳይ ለመምከር በመታደላቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም በሀገራዊ ምክክሩ የነቃ ተሳትፎ በማድረግና ይህንን ታሪካዊ እድል በመጠቀም ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ስንዱ ቤተማርያም፤ ሁሉንም በማሳተፍ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ሰላምን ለማጽናትና ሀገርን ለመገንባት ወሳኝ በመሆኑ ተሳትፏችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ተደራሽነትና አጋርነት ከፍተኛ ባለሙያ ፍሬሰናይ ገበየሁ፤ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ ከሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር የተውጣጡ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የመድረኩ ዓላማም የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ሀሳብና አስተያየት በማከል ለምክክር ሂደቱ መሳካት ድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ዓላማ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ዋና ዋና ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት መሆኑ ይታወቃል።