ቀጥታ፡

የመምህርነት ሙያን በመደገፍ ተመራጭ እንዲሆን ማድረግ ይገባል-የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር

አዲስ አበባ፤መስከረም 26/2018 (ኢዜአ)፡-የሙያዎች ሁሉ ቁንጮ የሆነውን መምህርነት በመደገፍ ተመራጭ እንዲሆን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አስገነዘበ።

የዓለም አቀፍ መምህራን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል እና የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ከዛሬ ጀምሮ የመምህራን ቀን በአዳማ ሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ይካሄዳል።

ቀኑን ምክንያት በማድረግ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ፣ኮንፈረንሶች እንደሚካሄዱ እና የዓመቱ ምርጥ መምህር/ት ወይም አሰልጣኝን በውድድር በመለየት ሽልማት እንደሚኖር ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ከመከበሩ ቀደም ብሎ ከፈረንጆቹ ጥቅምት 1 እስከ 3 እንደ አኅጉር በአፍሪካ ኅብረት የመምህራን ቀን መከበሩን አውስተዋል።

ጥሩ ዐቅምና ውጤት ያላቸው ሙያውን በስፋት ባለመቀላቀል እና ከሙያው ክብደት አንጻር ለዘርፉ የሚደረግ ማበረታቻ ውስን መሆን እየተፈተነ ላለው ሙያ የመምህራን ቀን መከበር አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ለትምህርት ጥራትና ብቁ መምህራንን ለማፍራት ብሎም በሙያው ለማቆየት በሀገር አቀፍ ደረጃ መምህራን የሚመሰገኑበት መድረክ በስፋት እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

ማንም ሰው ባይማር ኖሮ አሁን ላለበት ስኬት አይደርስም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ትምህርት መሠረት ነው፤ ይህን መሠረት የሚገነቡት ደግሞ መምህራን ናቸው ብለዋል።

መምህርነት ሁሉንም ሙያዎች አምራች እንደመሆኑ ሙያውን ከማሳደግ አንጻር ብዙ ማበረታቻዎች መኖር አለባቸው፤ ሙያውን ካልደግፍነው ሌሎች ሙያዎች ሁሉ ጉዳት ላይ ይወድቃሉ ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም