ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የማር ምርት ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ደረጃ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያን የማር ምርት ጥራት ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ደረጃ (ስታንዳርድ) ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።   

ኢኒስቲትዩቱ በተባበሩት መንግሥት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ትብብር በንብ ማነቢያ ቀፎ፣ የማር ምርት ማሸጊያና ማጓጓዥያ ደረጃ (ስታንዳርድ)  ዙሪያ የግብዓት ማሰባሰቢያ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው። 


 

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንድማገኝ አሰፋ÷ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ኢትዮጵያ የማር ምርት ጥራትና ዓለም አቀፍ የተወዳዳሪነት ደረጃን የሚያሳድግ አቅም አላት። 

የኢትዮጵያ ባህላዊ የማር ምርታማነት አሰራሮችና ባዕድ ነገሮች የመቀላቀል ያልተገባ ድርጊት በዘርፉ የእሴት ሰንሰለት ላይ ጫና በማሳደር ከዘርፉ ከሚጠበቀው ደረጃ ጥቅም እንዳይገኝ ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና አባልነትና የዓለም ንግድ ድርጅት አባል የመሆን ጉዞ በውጤታማነት ለመምራትም የኢትዮጵያን ምርቶች ጥራት የማስጠበቅ ጉዳይ ትኩረትን እንደሚሻ ተናግረዋል።

በዚህም ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ጋር በመተባበር የንብ ማነቢያ ቀፎ፣ የማር ምርት ማሸጊያና ማጓጓዣ ላይ አስገዳጅ ደረጃ (ስታንዳርድ) መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የማር ምርታማነት ደረጃውም አስገዳጅ የአመራረት መስፈርቶችን በማካተት ጤንነቱና ደኅንነቱ የተጠበቀ ማር ለማምረት እና ዘመናዊ የማር አቆራረጥ ሥርዓትን መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።  

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት የደረጃ ዝግጅት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ይልማ መንግሥቱ÷ በማር አመራረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ጥራት የጎደላቸው ቁሳቁሶች የምርት ጥራትን ያጓድላሉ ብለዋል።


 

አስገዳጅ ደረጃ (ስታንዳርድ) በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በዘላቂነት በመፍታት የማር ምርት ጥራትና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።  

የማር ምርት ጥራት አስገዳጅ ደረጃን (ስታንዳርድ) ለብሔራዊ ደረጃዎች ቦርድ አቅርቦ በማጸደቅ በተያዘው በጀት ዓመት ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።  

የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አሰግድ አዳነ÷ የኢትዮጵያን የማር ምርት ጥራት፣ ተወዳዳሪነትና የገበያ ተደራሽነት የሚያሳድግ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

ለንብ አናቢ አርሶ አደሮች በማር አመራረት ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት፣ለማር ምርት የሚያገለግሉ ዘመናዊ ቁሳቁሶች ድጋፍ በማድረግ በኩልም ውጤታማ ተግባራት መከናወኑን አስረድተዋል።   

በተባበሩት መንግሥት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዓለም አቀፍ የገበያ ተደራሽነት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሰለሞን መንገሻ÷ የኢትዮጵያን ተስማሚነትና ምዘና የላቦራቶሪ አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ድጋፎች እየተደረገ ነው ብለዋል።


   

የማር ምርት ናሙናዎችን በሀገር ውስጥ ማድረግ የሚያስችል የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው የባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።  

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው አውደ ጥናት ላይ የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም