ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህርዳር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ከፈቱ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህርዳር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018 (ኢዜአ):-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህርዳር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሉቱ በመጀመሪያው ዙር 12 ተቋማት በርካታ አገልግሎት የሚሰጡባቸውን 52 መስኮቶች ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ማሻሻያውን መሰረት አድርጎ ከፌደራል ጀምሮ በሁሉም ክልሎች እየተተገበረ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዘመናዊ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ከቀደምቶቹ ውስጥ መሆኗን አውስተው፥ ነገር ግን ሌሎች ሀገራት እየሰጡ ካሉት ዘመናዊ አገልግሎት አንፃር በብዙ ርቀት ወደኋላ መቅረቷን ጠቅሰዋል።
ይህን የአገልግሎት ችግር ለመቅረፍ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መተግበሩን ጠቅሰዋል።
መሶብ ባለሙያንና ቴክኖሎጂን በማጣመር ጊዜና ገንዘብን በመቆጠብ የአገልግሎት ቅልጥፍናን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
ብልፅግናን ለማረጋገጥ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ ማምጣት የግድ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
መሶብ የተማረ የሰው ኃይል ይፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዲጂታል ስርዓቱ ችግር ባጋጠመው ቁጥር አገልግሎት የለም የሚል አካሄድ ከዚህ በኋላ መኖር የለበትም ብለዋል።
መንግስት የተሟላ መሠረተ ልማት በመዘርጋትና ብልሽት ሲያጋጥም በራስ አቅም ፈጣን መፍትሔ የሚሰጡ ሙያተኞችን ለማብቃት እንደሚሰራ በመግለጽ መሠረተ ልማቶችን ከውድመት መጠበቅ የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል።
ለችግሮች እልባት እየሰጡ ሁልጊዜም ለህብረተሰቡ ፈጣን አገልግሎትን ባልተቋረጠ መልኩ መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል።
በኮሪደር ልማት ላይ ያለው 24 ሰዓት የመስራት ባህል በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትም መደገም እንዳለበት ነው ያስረዱት።
የመንግሥት አገልግሎትን እስከ ቀበሌ ድረስ በማውረድ ወደ ህዝቡ በመቅረብ እርካታን መጨመር እንደሚገባም እንዲሁ።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ የፌደራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።