የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሀገር ደረጃ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ውጥኖች እየተከናወኑ ባለበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል - የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ ተሣታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሀገር ደረጃ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ውጥኖች እየተከናወኑ ባለበት ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል - የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ ተሣታፊዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018 (ኢዜአ):-የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሀገር ደረጃ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ውጥኖች እየተከናወኑ ባለበት ወቅት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው የሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ ተሣታፊዎች ገለጹ፡፡
የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል " ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት " በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በአዲስ አበባ ሆረ ፊንፊኔ እና ዛሬ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆረ ሀርሰዴ ተከብሮ በስኬት ተጠናቋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የቢሾፍቱ ሆረ-ሀርሰዴ የበዓሉ ታዳሚዎች ኢሬቻ ከክረምት ወቅት መለያየትና መራራቅ በኋላ ሰዎች በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት በዓል ነው ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊ አቶ ጉዮ ቦሩ የዘንድሮው ኢሬቻ በዓል መንግስት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ባጠናቀቀበት ጊዜ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በሀገር ደረጃ ሌሎች ውጤታማ የልማት ፕሮጀክቶች መጀመራቸውም የብልጽግናን ጉዞ ከዳር እንዲደርስ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢሬቻን በጎ እሴት ለአብሮነት ማጠናከሪያ በማዋል የተጀመሩ የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ጠቁመዋል፡፡
ኢሬቻን ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴቶችን በማጠናከር በመንግስት የተጀመሩ ለትውልድ የሚተርፉ የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሲፈን ረጋሳ ናቸው፡፡
ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ በዓል ሳይሆን ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት የጋራ እሴት መሆኑን ጠቁመው፤ አብሮነት የሚጸናበት በዓል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ ፍቃዱ ባይሳ ሀገራዊ ለውጡ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ባህሎች እንዲጎለብቱ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች በየአካባቢው ትልቅ ለውጥ እየታየ መሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በቢሾፍቱ ከተማ የተመለከቱትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን አክለዋል።