ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ፖሊስ የተደራጁ ወንጀሎችን እና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ፖሊስ የተደራጁ ወንጀሎችን እና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቀላሉ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ የተወሰደውን ቁርጠኝነት የሚያሳኩ ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረው የሪፎርም ሥራ ዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያና የአዲስ ሕንጻ ምረቃ መርሃ ግብር ተካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽር ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የክልሉ ፖሊስ የክልሉን ህገ መንግስት ለማስከበር እና ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ቀን ከሌት እየሰራ ይገኛል።

የክልሉን የልማት ፕሮጀክቶች ለማሳካት ጠቅላይ መምሪያው ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በተወሰደ ህግ የማስከበር ስራ ተግባር ሰላምን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ቴክኖሎጂ መር ዘመናዊ የወንጀል ምርመራ ሂደት እንዲጠናከር እየተሰራ መሆኑንን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉን ፖሊስ ክልሉ አሁን ያለበትን የሰላምና የልማት ጥያቄዎች ሊመልስ በሚችል መልኩ ለማደራጀት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተከናወነው ተቋማዊ ሪፎርም ፖሊስ የአሠራር ነጻነት እንዲኖረው መደረጉን ጠቁመው፤ ተጠሪነቱ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሆኑ ለለውጥ ሥራዎች መሠረት ጥሏል ብለዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የክልሉ ፖሊስ የተደራጁ ወንጀሎች እና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ተቋሙ ዘመናዊ አሰራርን እንዲተገብር የዲጂታል እና ተመሳሳይ ዘመናዊ አሰራሮችን እንዲከተል እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ሰራዊት አባላት በሙያ ስነ ምግባር፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በወንጀል ምርመራ ቴክኖሎጂና በፎረንሲክ ሳይንስ ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ዛሬ የተመረቀው ሕንጻም በወንጀል መከላከል እና ምርመራ እንዲሁም ለአጠቃላይ ዘመናዊና ተቋማዊ ልህቀት እየተሰራ መሆኑን እንደሚያመላክት ጠቅሰዋል፡፡

ፖሊስ ሕዝባዊ ቅቡልነት እንዲኖረው እየተደረገ ያለው ጥረት ለውጥ እያሳየ ነው ያሉት ኮሚሽር ዘላለም (ዶ/ር)፤ በሪፎርም ሥራዎች ዘመናዊ የወንጀል ምርመራ ሂደት እንዲጠናከር እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በደብረብርሃን ከተማ የጀግኖች ማዕከል ግንባታ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በህግ ማስከበር ስራ ለተሰማሩ የፖሊስ አባላት በቅርቡ ዕውቅና እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡

በመጨረሻም ለክልሉ ፖሊስ ስኬታማ ስራ እገዛ ያደረጉ ባለድርሻ አካላት በክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ስም አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም