የአማራ ክልል ፖሊስ የማይናወጥ የህዝብ አገልጋይና የህግ አስከባሪ ተቋም የሚያደርገውን የለውጥ ጉዞ ጀምሯል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ፖሊስ የማይናወጥ የህዝብ አገልጋይና የህግ አስከባሪ ተቋም የሚያደርገውን የለውጥ ጉዞ ጀምሯል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ፖሊስ የማይናወጥ የህዝብ አገልጋይና የህግ አስከባሪ ተቋም የሚያደርገውን የለውጥ ጉዞ ጀምሯል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ተቋሙ የጀመረውን ሪፎርም፣ የዲጂታላይዜሽን ሥራና አዲሱን የዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ መርቀናል ብለዋል።
የአማራ ክልል በሁለት ግንባር፣ ከጥፋት ኃይሎች እና ከድህነት ጋር ተዋግቶ ሁለቱንም በማሸነፍ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
ክልሉ ደረጃ በደረጃ ሁለቱንም በመርታት ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ክልል ፖሊስ አዲስ የለውጥ ጉዞ ስኬትም አንዱ የድል ምልክት ነው ብለዋል።
የክልሉ ፖሊስ የወንጀል መከላከልና የምርመራ አቅሙን ለማላቅ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተደራጀ፣ በሙያዊ ታማኝነትና በላቀ የህዝብ አገልጋይነት እሳቤ የተቃኘ ዘመናዊ አሠራር እየዘረጋ ይገኛል ነው ያሉት።
የተቋሙ የለውጥ ጉዞ መዳረሻ ከህንፃና ከዲጂታል መሠረተ ልማት የተሻገረ፣ ህዝብን ከጥፋት ኃይሎች የመጠበቅ እምነትን መገንባት፣ ህግና ፍትሕን ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ፖሊስ ለሕዝቡ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በሃይማኖት ጣልቃ የማይገባ፣ ከሌብነት የጸዳ እና ጎጠኝነትን የሚጸየፍ ሊሆን ይገባዋል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ሪፎርሙም እነዚህን በማሳካት ደማቅ ታሪክ የሚፅፍ የፖሊስ ኃይል ማፍራት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሳካም ሙሉ ዕምነት አለኝ ብለዋል።