የአማራ ክልል መንታ ትግል በማድረግ የሰላምና የብልፅግና ድል እያስመዘገበ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል መንታ ትግል በማድረግ የሰላምና የብልፅግና ድል እያስመዘገበ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል መንታ ትግል በማድረግ የሰላምና የብልፅግና ድል እያስመዘገበ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ፖሊስ የጀመረውን የሪፎርም ሥራ፣ የዲጂታላይዜሽንና አዲስ የዋና ጠቅላይ መምሪያ ህንፃ መርቀዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የአማራ ክልል በመንታ ተጋድሎ ላይ ያለ ክልል መሆኑን ጠቅሰው፤ በአንድ በኩል ከጽንፈኛ፣ ከባንዳና ከባዳ ጋር በሌላ በኩል ብልጽግናን ለማምጣት ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ጋር እየታገለ ነው ብለዋል።
ክልሉ መንታ ትግል አድርጎ መንታ ድል እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአማራ ክልል ፖሊስ የሪፎርም ሥራ የዚህ መንታ ድል አንዱ መገለጫ እንደሆነ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ በክልሉ ያሉ ዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ አያሌ መስዋዕትነቶችን መክፈሉን አውስተዋል።
ከወንጀለኞች፣ ከጽንፈኞች፣ ከሙሰኞች፣ ከኮንትሮባንዲስቶች፣ ከባንዳዎችና ከባዳዎች ጋር ተፋልሟል ነው ያሉት።
የክልሉ ፖሊስ ሀገራዊና ክልላዊ ዕድገትን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ኃይላት መጠንና ዓይነትም የመጨመሩ አይቀሬነት ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የተከናወነው ሪፎርም ብቁ አደረጃጀት፣ አሠራርና ገለልተኛ የፖሊስ ዶክትሪን የሚከተል ተቋም መፈጠሩን፣ የዞን ፖሊስ መምሪያ እና የወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶችን ቢሮዎች ለሥራ ምቹ ለማድረግም እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የሥራ ቦታዎችን ለአሠራርና ለአገልግሎት ምቹ የማድረግና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሕግና ሥርዓትን የማስከበር፣ ግጭቶችን የመከላከልና ሕገ ወጥ የወንጀል ድርጊቶችን የመቆጣጠር ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሠራ ነው ብለዋል።
ከዜጎች የሚቀርቡ ጥቆማዎችን በፍጥነት በመቀበል አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራርና አደረጃጀት ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱን አመልክተዋል።
ፖሊስ በአመለካከት መለወጥ አለበት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለቆመለት ዓላማና መለዮ ዝግጁ የሆነ ፖሊስ ለመገንባት የአመለካከት ለውጥ የግድ መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊስ ለሕዝቡ አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በሃይማኖት ጣልቃ የማይገባ፣ ከሌብነት የጸዳ እና ጎጠኝነትን የሚጸየፍ ሊሆን እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ክልሉን ከባዳና ከባንዳ ተከላክሎ ለዕድገት በማብቃት፣ ላመነበትና ቃል ለገባለት ተልዕኮ መሥዋዕትነት በመክፈል እንዲሁም ልቡ፣ አስተሳሰቡና እጁ ከጽንፈኝነት፣ ከጎጠኝነት፣ ከሌብነት የጸዳ በመሆን ደማቅ ታሪክ መፃፍ አለበት ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ አሁን የጀመረውን ሪፎርም በፈጠራና ፍጥነት በማቀላጠፍ ክልሉን የሚመጥን የፖሊስ ኃይል መገንባት የግድ መሆኑን በአፅንኦት ገልጸዋል።
የአማራ ክልል እንዳይረጋጋ የማይጠቅም የፖለቲካ አካሄድ የህዝቡን ማህበራዊ ኢኮኖሚ የሚገድቡና በትውልድ ላይ እየቆመሩ ያሉ አካላት የያዙት አካሄድ አጥፊ መሆኑንና እንደማያዋጣቸው ሊያውቁ ይገባል ብለዋል።
መንግሥት ለሠላም እጁን በተደጋጋሚ ዘርግቷል፤ ታጣቂዎች ወደ ሠላም እየመጡ መሆናቸውን ተናግረው፤ አሁንም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወደ ሰላም ሊመጡ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የማይቀበሉ አካላት ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የራሱን ህዝብ መበደል እንዲሁም ህዝባችንን ለበደለ አካል መላላክ በታሪክ የሚያስወቅስ ነው ብለዋል።
የፖሊስ ሪፎርም ታሪካዊ ወቅታዊና አስደማሚ መሆኑን ገልጸው፤ የክልሉ ፖሊስ የጀመረው ሪፎርም እንዲሳካ የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።