በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የቡታጅራ ካምፓስ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራውን ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የቡታጅራ ካምፓስ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራውን ጀመረ

ቡታጅራ ፤ መስከረም 25/2018 (ኢዜአ)፡-በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የቡታጅራ ካምፓስ መደበኛ የመማር ማስተማር ስራውን ጀምሯል፡፡
በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንዳሉት መንግሥት ጥራት ያለውን ትምህርት ተደራሽ በማድረግ በእውቀት የበቁ ዜጎችን ለማፍራት የትምህርት ተቋማትን የማጠናከር ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡
ጠንካራና የተደራጀ የትምህርት ተቋምን መፍጠር የሀገርን ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል።
የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ቡታጅራ ካምፓስ በእውቀት የበቁ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ገልፀዋል፡፡
መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ቀርፆ እየተገበረ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመርቃ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት ስለመጀመሯም ጠቁመዋል፡፡
በሀገር የተጀመሩ የእድገትና የብልፅግና ውጥኖችን በመደገፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የትምህርት ዘርፉን ማጠናከር እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በመማር ማስተማር፤ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅና ተደራሽነትን በማስፋት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር በቡታጅራ የመማር ማስተማር ስራዉን መጀመሩ ተናግረዋል።
"የአካባቢው ማህበረሰብ ለትምህርት ካለው ተነሳሽነት የተነሳ የወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በቡታጅራ ካምፓስ እንዲከፍት ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲነሳ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ናቸዉ፡፡
ዛሬ የመማር ማስተማር ስራውን እንዲጀምር የተደረገው የቡታጅራ ካምፓስ የማህበረሰቡን የትምህርት ደረጃ ለማሻሻል አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፋሬስ ደሊል (ዶ/ር) እንደገለፁት ኢትዮጵያ በመካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት ጥራት ያለዉ ትምህርት ተደራሽ ማድረግ ይገባል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመቅረፍ በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርስቲዉ በቡታጅራ ከተማ የከፈተዉ ካምፓስ በአካውንቲንግ፤ በቢዝነስ፡ በማኔጅመንትና በማርኬቲንግ ትምህርት ክፍሎች የተመደቡ 200 ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ዙር ተቀብሎ ማስተማር ጀምሯል፡፡
ካምፓሱ የአካባቢውን ማህበረሰብ የትምህርት ፍላጎት የማሳካት፤ የማህበረሰቡን ችግር የመፍታትና የጥያ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርስን የማስተማሪያና የምርምር ማዕከል እንዲሆን እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በመርሐ ግብሩ የክልል የጉራጌና የምስራቅ ጉራጌ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡