አረንጓዴ አሻራ ብዝኃ ሕይወትን በማስጠበቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ ብዝኃ ሕይወትን በማስጠበቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018 (ኢዜአ):-አረንጓዴ አሻራ የብዝኃ ሕይወትን በማስጠበቅ የምግብ ሉዓላዊነትንና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ዕድል መፍጠሩን የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ዕቅድ ለማሳካት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካርታ ካስኬ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ስራ ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በውሃና አፈር ጥበቃ ስራ ስነ-ምህዳርን በማስተካከል ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የተሻሻሉ ዝርያዎችን የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ስነ-ምህዳርን በመጠበቅ ዘላቂነት ያለው የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የክልል ቢሮ ሀላፊዎች በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ አይነተኛ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይፈዲን ማሃዲ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጎዳውን ስነ- ምህዳር መልሶ እንዲያገግም ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ተክሎች በስፋት በመተከላቸው የሚታይ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል የአካበቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መንገሻ አውራሪስ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብዝኃ ሕይወትን በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የተሰሩ ስራዎች የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ አስችሏል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የደንና የአካባቢ ጥበቃ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አብርሃም መጫ በበኩላቸው፤ አረንጓዴ አሻራ የብዝኃ ሕይወትና ስነ-ምህዳርን በማሻሻል ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡