ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብት በመሆኑ የሁሉም ተሳትፎ ይጠበቃል 

አሶሳ፤ መስከረም 25/2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብት በመሆኑ የሁሉም ተሳትፎ እንደሚጠበቅ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

"የሴቶች፣ የወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የውይይት መድረክ ተጠናቋል።


 

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ሀገራዊ ምክክር አለመግባባቶችን የሚፈታ እና ለችግሮች መፍትሄ የሚያመጣ በመሆኑ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት ወይዘሮ አዳነች አስራት ለኢዜአ እንደገለጹት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ የምክክር ሂደቱ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው።


 

አካል ጉዳተኞች የምክክሩ ተሳታፊ መሆናቸው ለችግሮቻቸው መፍትሔ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ  በሀገር ጉዳይ እኩል የመወሰን ዕድል እንዲሰጣቸው ያደርጋቸዋል ብለዋል።

በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች አካል ጉዳተኞችን ለከፋ ጉዳት የሚዳርጉ በመሆናቸው ችግሮቹን በምክክር በመፍታት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ አካባቢ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ክብሮም ገብረመድህን በበኩሉ፣ ሀገራዊ  ምክክሩ  ወጣቶች በሀገር ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ በሠላም ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጿል።


 

ስብዕና በመገንባት ወጣቶች አብሮነትን እና ህብረብሄራዊነትን እንዲያጠናክሩ ማድረግ እንደሚገባ ተናግሯል።

በመድረኩ ላይ የነበረው የቡድን ውይይት የምክክሩን አስፈላጊነት እና ፅንሰ ሃሳብ የበለጠ እንድንረዳ አግዞናል ብሏል።

የምክክር ሂደቱ ተቀራርቦ መስራትን የሚያጎለብትና ማህበራዊ እሴቶችን የሚያጠናክር በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊሳተፍበት ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ከልቱም ባበክር ናቸው።


 

በተለይ ሴቶች የምክክር ሂደቱ ሃሳባቸውን የሚያንፀባርቁበት ለሠላም ያላቸውን አቋም የሚያሳዩበት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ሴቶች የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም በምክክሩ አስፈላጊነትና ሂደቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን በበኩላቸው፤ ምክክር ለዘላቂ ሠላም እና ለሀገር ግንባታ ያለውን ፋይዳ ዜጎች ግንዛቤ ይዘው የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።


 

የውይይት መድረኩ የተሳታፊዎች የነቃ ተሳትፎ የታየበት ነበር ያሉት ኮሚሽነሯ ለምክክሩ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች መነሳታቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም