በቅድመ መከላከል ሥርዓት ህብረተሰቡ የልብና ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ሥርጭቶችን መቀነስ ይኖርበታል - ዶክተር ከፈለኝ ደጀኔ - ኢዜአ አማርኛ
በቅድመ መከላከል ሥርዓት ህብረተሰቡ የልብና ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ሥርጭቶችን መቀነስ ይኖርበታል - ዶክተር ከፈለኝ ደጀኔ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018 (ኢዜአ):-በቅድመ መከላከል ሥርዓት ህብረተሰቡ የልብና ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ሥርጭቶችን በመቀነስ ጤናውን መጠበቅ እንደሚኖርበት የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል የውስጥ ደዌ እና የልብ ሃኪም ዶክተር ከፈለኝ ደጀኔ አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል የውስጥ ደዌና የልብ ኃኪም ዶክተር ከፈለኝ ደጀኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የልብና የደም ሥር እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ የሽታዎች አይነቶች በቀዳሚነት ሞትን እያስከተሉ ነው ።
በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ የሞት ምጣኔ ከሚያስከትሉ የበሽታ አይነቶች ውስጥ የልብና ደም ስር በሽታ አንድ ሶስተኛውን እንደሚይዙም የዓለም ጤና ድርጅት መረጃዎችን በማጣቀሻነት ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም የልብና የደም ሥር እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ አይነቶች ሥርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።
ልብ ኦክስጂን ያለውን ደም መርጨት ዋነኛ ተግባሩ የሆነ የሰውነት ክፍል ነው ያሉት ዶክተር ከፈለኝ ደጀኔ፤ የልብ የሰውነት ክፍል መስተጓጎልም በጤና ላይ ከባድ እክልን ያስከትላል ብለዋል።
የድካም ስሜት፣ ሰውነት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ማዞርና መሰል ምልክቶች ከተስተዋሉ የልብ ጤና አክል ምልክቶች መሆናቸውን በመገንዘብ የጤና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተለይም የልብ ምት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር፣ ድንገተኛ የደረት ውጋት ስሜት፣ ትኩሳት፣ ኢንፌክሽንና መሰል ምልክቶች ደግሞ አፋጣኝ የልብ ህክምና የሚጠይቁ መሆናቸውን አሳስበዋል።
የልብ ህመም በተፈጥሮና ከውልደት በኋላ የሚከሰት ቢሆንም ከቅድመ መከላከል ችግር የሚመነጩ የተለያዩ የልብ ህመም አጋላጭ መንስኤዎች መኖራቸውን አስረድተዋል።
በዋናነትም የጉሮሮ ቁስለት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ጫት መቃም፣ ከመጠን ያለፈ አልኮል መጠጣት፣ ጨውና ቅባት የበዛበት የአመጋገብ ሥርዓት ከብዙ በጥቂቱ የልብ ህመም አጋላጭ መንስኤዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በዚህም ህብረተሰቡ የጤና ምርመራ እና የቅድሞ መከላከል የጤና ሥርዓትን ባህል በማድረግ የልብ ጤንነትን መጠበቅና መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡም በየጊዜው የቅድመ ጤና ምርመራ የማድረግ ባህሉን በማዳበር እራሱን ተላላፊ ካልሆኑ የበሽታ አይነቶች መጠበቅ እንደሚኖርበትም መክረዋል።
የልብና የደም ሥር የጤና አጋላጭ ምልክቶች ከተስተዋሉም ወደጤና ተቋም በማቅናት ህክምና ማድረግ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።