ማንችስተር ሲቲ ከብሬንትፎርድ ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ማንችስተር ሲቲ ከብሬንትፎርድ ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 25/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ በጂቴክ ኮሙኒቲ ስታዲየም የሚካሄደው የብሬንትፎርድ እና ማንችስተር ሲቲ ጨዋታ ከዛሬ መርሃ ግብሮች መካከል ተጠቃሽ ነው።
ብሬንትፎርድ በሰባት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ማንችስተር ሲቲ በ10 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
ቡድኖቹ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሲገናኙ የዛሬው ለዘጠነኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ አምስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ብሬንትፎርድ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
በጨዋታዎቹ ማንችስተር ሲቲ 12 እና ብሬንትፎርድ 7 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ሁለቱ ክለቦች በስድስተኛ ሳምንት ካስመዘቧቸው ድሎች በኋላ በአሸናፊነት ጉዞ ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ መሆኑ ተጠባቂ ያደርገዋል።
የ39 ዓመቱ ዳረን ኢንግላንድ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በተያያዘም ኤቨርተን ከክሪስታል ፓላስ፣ ኒውካስትል ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ ዎልቭስ ከብራይተን እና አስቶንቪላ ከበርንሌይ በተመሳሳይ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።