ቀጥታ፡

ኢሬቻ ሆረ ሀረሰዴ በዓል ልዩና አስደናቂ ነው - የበዓሉ ተሳታፊ የሆኑ የአየርላንድ ዜጎች

ቢሾፍቱ ፤ መስከረም 25/2018(ኢዜአ)፦ ኢሬቻ ሆረ ሀረሰዴ በዓል ልዩና አስደናቂ ነው ሲሉ የበዓሉ ተሳታፊ የሆኑ የአየርላንድ ዜጎች ገለፁ።

የሆረ ሀረሰዴ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ በርካታ ታዳሚዎች ከሌሊቱ ጀምሮ የተገኙ ሲሆን፣ ሥነ ሥርዓቱ በአባ ገዳዎች ምርቃት ተጀምሯል።

የበዓሉ ተሳታፊዎች ውብና ማራኪ በሆኑ ባህላዊ አልባሳትና እሴቶች አሸብርቀው፣ ባህላዊ ጭፈራዎችንና ልዩ ልዩ ዜማዎችን በማዜም በሆረ ሀረሰዴ በማቅናት በዓሉን በድምቀት እያሳለፉ ይገኛል።

በበዓሉ ለመታደም ከአየርላንድ የመጣው ናኤል የኢሬቻ በዓል እጅግ አስደናቂ እና አስደማሚ ነው ብሏል።


 

በሚታየው የባህላዊ ልብሶች ድምቀት እጅግ በጣም መማረኩን ገልጿል።

የኢሬቻ በዓል ፍጹም ልዩ እና ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቅ አስደናቂ ገጠመኝ እንደሆነ የተናገረው ናኤል፤ በነበረው ትይንት ተማርኬያለሁ ሲል ገልጿል።

ኢሬቻ የኢትዮጵያ ባህል ምን ያህል የበለፀገ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጾ፣ የሚመለከታቸው አካላት በዓሉን በዓለም ዙሪያ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው ተናግሯል።

ሌላኛዋ አስተያየት የሰጠችን ኦርና በበሉ ላይ እድል አግኝታ በመታደሟ መደሰቷን ገልፃለች።


 

በበዓሉ ላይ በተመለከተቻቸው ደማቅ ባህላዊ አልባሳት፣ ባህላዊ ጭፈራዎችና ልዩ ልዩ ዜማዎች በጣም እንደተማረከች ተናግራለች።

በዓሉ በጣም አስደናቂ እና በዓለም ላይ ካሉ ክብረ በዓሎች ልዩ እንደሆነም ነው የገለፀችው ።

የኢትዮጵያ ህዝብ አቀባበልና ደግነት እጅግ በጣም አስደናቂ እንደሆነ ገልጻ ይህም በዓሉን በልዩ ስሜት ለማክበር እንዳስቻላት ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም