ክልላዊ የልማት ስኬቶችን ለማስቀጠል የአመራሮችን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ክልላዊ የልማት ስኬቶችን ለማስቀጠል የአመራሮችን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 24/2018(ኢዜአ)፦ ክልላዊ የልማት ስኬቶችን ለማስቀጠል የአመራሮችን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት መሰጠቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሦስት ቀናት ለአመራሮች ሲሰጥ የቆየው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፣ በክልል የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን ለማዝለቅ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል።
ይህን እውን ለማድረግም የአመራሩን አቅም ማጎልበት ታሳቢ ያደረጉ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
አመራሩም በስልጠናው ያገኘውን ተጨማሪ ዕውቀት ሥራ ላይ በማዋል አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በተጨማሪም የህዝብን የልማት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ከባለሙያዎች ጋር የሚኖራቸውን ተግባቦት ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የክልሉ ስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አማኑኤል አብደላ ስልጠናው ለቀጣይ ስራቸው ስኬታማነት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ይህም በአካባቢያቸው ያሉ ሀብቶችን በአግባቡ ተጠቅመው የህዝብን የልማት ጥያቄ በተገቢው ምላሽ ለመስጠት መደላድል ይፈጥራል ብለዋል።
ስልጠናው የአመራር ሚናን በሚገባ ተረድተን ህዝቡን እንድናገለግል የመቻልን አቅም የፈጠረልን ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ጎበዜ ጎአ ናቸው።
አመራሩ ለህዝቡ ተገቢ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያግዝ በመሆኑ በስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ከአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው ስልጠና የክልል፣ የዞን እና የ3ቱ ሪጂኦ ፖሊሲ ከተሞች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።