ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 24/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ወደ ሥራ ማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አለምአንተ አግደው ገለጹ።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ወደ ሥራ ማስገባት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው በዚህ ወቅት እንደገለጹት የዳኝነት አገልግሎቱን ፈጣን፣ ተገማችና ጥራት ያለው ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በዚህም የመደበኛ የዳኝነት ስርዓቱን በማዘመን፣ የዳኞችን አቅምና ክህሎት በማሳደግና መብትና ጥቅማቸውን በማስጠበቅ የተጀመረው የሪፎርም ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ከመደበኛ የዳኝነትና የፍትሕ ሥርዓቱ ጎን ለጎን የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን እስከ ታች ድረስ በማቋቋም አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓት ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአዋጅ ቁጥር 298/2017 መሰረት ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን በተያዘው በጀት ዓመት እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለህብረተሰቡ በእርቅ ላይ የተመሰረተ፣ ግልጽ፣ ቀልጣፋና ተአማኒነት ያለው ፍትህ መስጠት የሚያስችሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም የአካባቢ መስተዳድሮች በተለይም የቀበሌ መዋቅሮች ባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ በማስተግበር በኩል የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።


 

የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የትራንፎርሜሽን ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሐናን አበበ ባቀረቡት ጽሁፍ እንደገለጹት ባህላዊ ዳኝነት ስርዓቱ የየአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የሚተገበር ነው።

ባህላዊ ዳኝነት አለመግባባቶችን በቀላሉና በመተማመን ፈትቶ ግንኙነትን ወደ ነበረበት የሚመልስ በመሆኑ ህብረተሰቡን ከወጪ የሚታደግ ነው ብለዋል።

በክልሉ ሽምግልና፣ አበጋር፣ መንታ ፍቅር የሚባሉና ሌሎች ባህላዊ የሽምግልና አይነቶች እንዳሉ ጠቁመው እነዚህን ባህሎች እውቅና በመስጠትና በማዘመን ውጤታማ ፍትህ ለማስፈን ይሰራል ብለዋል።

በመድረኩ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ አመራሮች፣ የፍርድ ቤት ዳኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም