ቀጥታ፡

የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስን በማልማት የገቢ ምንጭ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል

ቡኢ፤ መስከረም 24/2018 (ኢዜአ)፦ የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስን በማልማትና የገቢ ምንጭ በማድረግ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) አስታወቁ።

በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ የሚገኘውን የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ የሚገኝበት አካባቢን በማልማት የመስህብ ስፍራ ለማድረግ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።


 

ወጪውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ፣ ከባለሀብቱና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በተመረቀበትና ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ማግስት የጢያ ዓለም አቀፍ ቅርስ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ወደ ተግባር መግባቱ የተለየ ትርጉም አለው፡፡

መካነ ቅርሱ ረጅም ዕድሜ ቢኖረውም በተገቢው መንገድ ለምቶ ለጎብኚዎች ምቹ ሳይሆን መቆየቱን ጠቁመዋል።

በዚህም ከቱሪዝም ዘርፍ መገኘት የነበረበትን ገቢ ሳያስገኝ መቆየቱን አስታውሰው ዓለም አቀፍ መካነ ቅርሱን በማልማትና የገቢ ምንጭ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።


 

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ በበኩላቸው ቢሮው በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የገቢ ምንጭ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ በ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ እንደሚከናወንለት ጠቁመዋል፡፡

የግንባታ ሥራው ሆቴል፣ የተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎችን እንዲሁም የግብይት ማዕከላትንና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን አካቶ እንደሚከናውንም ተናግረዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን፤ የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ በሀገሪቱ ከሚገኙና በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዱና ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ ቅርስ ነው ብለዋል፡፡


 

በዞኑ የሚገኙትን ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኝን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

የጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ ለጎብኚዎች አመቺ በሆነ መልኩ ሳይለማ መቆየቱ የተናገሩት የቡኢ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ በቀለች ደጋጋ አሁን ስፍራውን ለማልማት ወደ ስራ በመገባቱ ደስተኛ መሆናቸው ተናግረዋል።

ለአካባቢው ስራ አጥ ወጣቶችና ለማህበረሰቡ የሥራ ዕድልና ሌሎች አማራጮችን ይዞ እንደሚመጣም ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞንና የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ ባለሀብቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም