ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች ለሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ ታዳሚዎች ላደረጉት የሞቀ ቤተሰባዊ አቀባበል ምስጋና ይገባቸዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች የሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ለመጡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች የሞቀ አቀባበል በማድረጋቸው ምስጋና ይገባቸዋል ሲሉ የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ ገለጹ፡፡

የቱለማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደውን የ2018 ዓ.ም ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል መጠናቀቁን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አባ ገዳ ጎበና በመግለጫቸው፣ ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦች በጉጉት የሚጠብቁት ኢሬቻ በሆራ ፊንፊኔ በድምቀት ተከብሯል ብለዋል። 


 

ኢሬቻ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ቋንቋና ባህል በድምቀት ያከበሩት መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የአንድነት፣ የመተባበርና የሰላም መገለጫ በሆነው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ላይ ከኢትዮጵያውያን አልፎ በርካታ የውጭ ዜጎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ኢትዮጵያውያን ወንድማማችነታችንንና የጋራ እሴት ያለን መሆኑን ያሳየንበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የአንድነት የጥንካሬና የመከባበር እሴት ማሳያ ሆኖ በድምቀት መከበሩን ገልጸዋል፡፡

ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የጸጥታ ሀይሎች ብርድና ጸሀይ ሳይገድባቸው ሚናቸውን ተወጥተዋል ብለዋል።


 

ወደ ከተማዋ የመጡ የተለያዩ እንግዶችን የትራንስፖርት ችግር እንዳይገጥማቸው አውቶቡስ በማሰማራት አብሮነቱን ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ጤና ቢሮዎች ሊከሰቱ ለሚችሉ የጤና እክሎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስምሪት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በአምስቱም የመግቢያ በሮች ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ለመጡ የኢሬቻ ተሳታፊዎች ላደረገው የሞቀ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአጠቃላይ በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ላደረጉ የፌዴራል፣ የአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል መንግስት የከበረ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም