የዘንድሮው የኢሬቻ አከባበር አዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት የተዋበችበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የኢሬቻ አከባበር አዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት የተዋበችበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2018(ኢዜአ)፦ የዘንድሮው የኢሬቻ አከባበር አዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት የተዋበችበት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ ታዳሚዎች ገለጹ።
የሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የታደሙ እና ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ታዳሚዎች እንዳሉት፤ የዘንድሮ የኢሬቻ አከባበር አዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት የተዋበችበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት እንዲሁም የሕዝቦች አንድነት እና ትስስር የበለጠ የሚጠናከርበት ነው ብለዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አበበ ጎፌ እንዳሉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶቿ እና የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች ለበዓሉ ልዩ ድምቀት መስጠታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች በተጠናቀቁበትና ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት መከበሩ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
እንደታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁሉ አሁን በመንግስት የተጀመሩ ሌሎች ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አብዲ መሀመድ በበኩላቸው፤ የዘንድሮ ኢሬቻ አከባበር ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ የልማት ጉዞ በጀመረችበት ወቅት መሆኑ ያስደስታል ብለዋል።
አዲስ አበባ ከተማ በጣም ውብና ጽዱ መሆኗን ገልጸው፤ ሆረ ፊንፊኔ የሚከበርበት ቦታ በኮሪደር ልማቱ በመዋቡ ለበዓሉ ድምቀት መስጠቱን ተናግረዋል።
አቶ ታምሩ ደገፋ በበኩላቸው፤ የሀገሪቱ እድገት እውን እንዲሆንና የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ እርሳቸውም የበኩለችን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
አቶ ቦቄ ኤይ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ገጽታ በዚህ መልኩ መቀየሩ ሌሎች የልማት ስራዎችን ለማከናወን ትልቅ ተነሳሽነት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ሆረ ሀርሰዲ የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሐሳብ ነገ ይከበራል።