የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓልን ሁሉም በጋራ በማክበር አብሮነታቸውን አሳይተውበታል - አባገዳ ጎበና ሆላ - ኢዜአ አማርኛ
የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓልን ሁሉም በጋራ በማክበር አብሮነታቸውን አሳይተውበታል - አባገዳ ጎበና ሆላ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2018(ኢዜአ)፦ የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ከሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ተገኝተው በጋራ በማክበር አብሮነታቸውን አሳይተውበታል ሲሉ አባገዳ ጎበና ሆላ ገለጹ።
የቱለማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ የተከናወነውን የ2018 ሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል መጠናቀቁን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
አባ ገዳ ጎበና በመግለጫቸው፣ ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦች በጉጉት የሚጠብቁት ኢሬቻ በሆራ ፊንፊኔ በድምቀት ተከብሯል ብለዋል።
ኢሬቻ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ቋንቋና ባህል በድምቀት ያከበሩት መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት መከበሩን ገልጸዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የውጭ ዜጎች የተሳተፉበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ታላቁ ኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የጸጥታ ሀይሎች ብርድና ጸሀይ ሳይገድባቸው ሚናቸውን ተወጥተዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአምስቱም አቅጣጫዎች የመጡ የተለያዩ እንግዶችን የትራንስፖርት ችግር እንዳይገጥማቸው አውቶቡስ በማሰማራት የጎላ ሚና መወጣቱን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ላደረጉ የፌዴራል፣ የአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል መንግስት የከበረ ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የአንድነት የጥንካሬና የመከባበር እሴት ማሳያ ሆኖ በድምቀት መከበሩንም አስታውቀዋል።