ቀጥታ፡

የክረምቱ ዝናብ በቀጣዩ ወርም ተጠናክሮ መቀጠሉ ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል- ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2018(ኢዜአ):-የክረምቱ ዝናብ በቀጣዩ ወርም ተጠናክሮ መቀጠሉ ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የረጅም ጊዜ የአየር ፀባይና የድርቅ ክትትል ዴስክ ኃላፊ በቃሉ ታመነ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የክረምቱ የአየር ፀባይ ትንበያ የዝናቡ ሁኔታ እንደሚራዘም የሚያመላክት ነው።

የክረምት ዝናብ በተለይ በሀገሪቷ የምስራቅ አጋማሽ አካባቢዎች ዘግይቶ የጀመረ ሲሆን፤ አወጣጡም ሊዘገይ እንደሚችል ነው የገለጹት። 


 

የአየር ሁኔታው ዘግይተው ዝናብ ባገኙ አካባቢዎች ተካሒዶ ለነበረው የእርሻ ስራ በተለይ ለሰብል እድገት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ደግሞ በህዳር ወር የአገሪቱ የሰሜን አጋማሽ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስለሚኖር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአየር ሁኔታው በደረሱ ሰብሎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ስለሚችልየሚሰጡ የአየር ትንበያዎችን  በመከታተል ጥንቃቄ መውሰድ ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው ለሆነ የሀገሪቱ የደቡብ አጋማሽ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ሊያገኙ ይችላሉ ነው ያሉት።

አሁን እየተገኘ ያለውን እርጥበት በአግባቡ መጠቀም የሚገባ ሲሆን፤ በማሳ ላይ የሚተኙ ውሃዎችን ማስወገድ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው፤ የበጋ ወቅት ትንበያ እንደሚያሳየው የዝናቡ ሁኔታ በቀጣዩ የጥቅምት ወርም እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።

ይኸው የዝናብ ሁኔታ ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች እድገት የሚጠቅም ሲሆን፤ የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።

የዝናቡ መራዘም ለእርሻ ስራው አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፤ በሰብል ላይ የተለየ ጉዳት እንደማይኖረውም ነው  የተናገሩት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም