በሀገራዊ ምክክር የሴቶች፣ ወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክር የሴቶች፣ ወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ኮሚሽኑ
ሐረር፤ መስከረም 24/2018(ኢዜአ)፡-በሀገራዊ ምክክር የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።
"የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ሚና እና አስተዋጽኦ ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ የውይይት መድረክ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ እንደሀገር የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በምክክር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
የምክክር ኮሚሽኑ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በአጀንዳ ልየታ፣ በምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን የመለየትና ሌሎች ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
ምክክር ኮሚሽኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የአጀንዳ ሃሳቦችን ባሰባሰበበት እና በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን በለየባቸው መድረኮች ወጣቶች፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ማሳተፉን ተናግረዋል።
በየመድረኩም የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና እገዛ ከፍተኛ እንደነበርም ኮሚሽነር ሙሉጌታ አመልክተዋል።
በተለያዩ አደረጃጀት ውስጥ የታቀፉ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ለልዩነቶች እና አለመግባባት መንስኤ የሆኑና ሀገራዊ መግባባት ሊፈጠርባቸው ይገባል ያሏቸውን የአጀንዳ ሃሳቦች በማደራጀት ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ስለኮሚሽኑና ስለምክክር ሂደቱ ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥ በማድረግ ትልቅ ሚና ማበርከታቸውን ጠቅሰው ይህ ትብብርና እገዛ ተጠናከሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በኮሚሽኑ የኮሚኒኬሽን ተደራሽነትና አጋርነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፍሬሰናይ ገበየሁ በበኩላቸው ለሁለት ቀን በሚዘልቀው የውይይት መድረክ ከሐረሪ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር የተውጣጡ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መድረኩ በአገራዊ የምክክር ሂደት ላይ በቂ ግንዛቤ በመፍጠር የሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞችን አበርክቶ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።