በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክር አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክር አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው
አሶሳ፤ መስከረም 24/2018 (ኢዜአ)፦ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክር አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድህን ገለጹ።
ኮሚሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ከሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ጋር በምክክሩ ሂደት ላይ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
በዚሁ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን፤ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክር አማራጭ የሌለው መፍትሄ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር በዘላቂነት ለመፍታት፣ ግጭትን ለማስወገድና ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የምክክር ሂደቱን አካታች፣ አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ለማድረግ ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ በተለይም የወጣቶች፣ የሴቶችና አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት በአሶሳ የሚካሄደው መድረክ "የሴቶች፣ የወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚቀጥል መሆኑም ታውቋል።