የመንግስት ድጋፍና በዘርፉ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የአምራች ኢንዱስትሪውን እያነቃቃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ድጋፍና በዘርፉ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የአምራች ኢንዱስትሪውን እያነቃቃ ነው
ሀዋሳ፤ መስከረም 24/2018(ኢዜአ)፦ የመንግስት ድጋፍና በዘርፉ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የአምራች ኢንዱስትሪውን እያነቃቃ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተናገሩ።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማበረታታት እና ውጤታማ ለማድረግ መንግስት የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ ጭምር እገዛና ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለመጨመርና የአምራች ዘርፉን ለማሳደግ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራሮች ታክሎበት እመርታዊ ለውጥ የታየበት ሆኗል።
በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ተከትሎ ከፍተኛ ማንሰራራት በማሳየት ምርታማነቱ ይበልጥ እያደገ እና ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በዘርፉ ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶች የመንግስት ድጋፍና በዘርፉ ልማት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ የአምራች ኢንዱስትሪው እየተነቃቃ መሆኑን ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች መካከል አቶ አለምገና ዘርጋው እና አቶ ያሬድ እስጢፋኖስ፤ ለዘርፉ ልማት መንግስት ለሰጠው ትኩረትና እያደረገ ላለው ድጋፍ አድንቀው የአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ሌላኛው በዘርፉ ልማት ላይ የተሰማሩት አቶ ወንደሰን ላንቃ፤ የዘርፉን ልማት ለማጠናከር ቀልጣፋ አሰራርን ከመዘርጋት ባለፈ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎችን በማመቻቸት ጭምር የታየውን ለውጥ አድንቀዋል።
በዚህም መሰረት የአምራች ኢንዱስትሪው ምርታማነት ፍላጎት፣ ጥራትና ብዛትን መሰረት አድርጎ እየተከናወነ በመሆኑ የሀገርን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ እያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልል አሁን ላይ ከ1 ሺህ 450 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ከክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።