የህዝብን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለዘላቂ ሰላም የበኩላችንን እንወጣለን - የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለዘላቂ ሰላም የበኩላችንን እንወጣለን - የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች
ባህር ዳር፤ መስከረም 24/2018 (ኢዜአ):-የህዝብን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለዘላቂ ሰላም መስፈን የበኩላቸውን እንደሚወጡ የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ወጣቶች መካከል ፈቃዱ አለምነው እንደገለጸው በከተማዋ ኮሪደርን ጨምሮ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ለህብረተሰቡ በተለይ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
በሃገር ደረጃም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከማስመረቅ ጎን ለጎን በርካታ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆናቸውንም አድንቋል።
ህብረተሰቡ ከሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ እንዳይሆን ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላትን እንደሚያወግዝ ገልጾ፣ በተለይ የትምህርት እንቅስቃሴን ለማስተጓጎልና መሰረተ ልማትን ለማውደም የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሴራ ለማክሸፍ ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚሰራ ተናግሯል።
ወጣቶች ግጭት ለማንም እንደማይጠቅም በመረዳት በሰላም ግንባታ ላይ በንቃት በመሳተፍ ሰላምን ለማስቀጠል ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግሯል።
በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠን ሰላም መሰረታዊ ጉዳይ ነው ያለው ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ንጋት አብነት ነው።
አሁን በአካባቢያቸው የመጣውን ሰላም ለማዝለቅ እሱን ጨምሮ ወጣቶች ከተማቸውን በንቃት መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግሯል።
በጫካ ያሉ የታጠቁ ሃይሎችም መንግስት በተደጋጋሚ ለሰላም ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ችግሮችን ተቀራርቦ በመነጋገር መፍታት እንዳለባቸው ተናግሯል።
የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ወጣት አበዜ ታከለ በበኩሏ የሀገር ዕድገትና ብልፅግና የሚረጋገጠው የተረጋጋ ሰላም ሲኖር መሆኑን ገልጻለች።
በመሆኑም ሰላም በዘላቂነት እንዲጠናከር በሰላም አስፈላጊነት ላይ ለአካባቢው ህብረተሰብ ግንዛቤን በመፍጠር የድርሻዋን እየተወጣች መሆኗን ተናግራለች።
ግጭት የሰው ህይወትን ከማጥፋትና በንብረት ላይ ውድመት ከማስከተል ያለፈ ጥቅም እንደሌለው ሁሉም ተገንዝቦ ችግሮችን በውይይትና በንግግር በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መስራት ይገባል ብላለች።