የቼልሲ እና ሊቨርፑል ተጠባቂ መርሃ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
የቼልሲ እና ሊቨርፑል ተጠባቂ መርሃ ግብር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ቼልሲ እና ሊቨርፑል ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።
የሁለቱ ቡድኖች መርሃ ግብር ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ይካሄዳል።
ቼልሲ በስምንት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሊቨርፑል በ15 ነጥብ የሊጉ መሪ ነው።
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሱ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በብራይተን እና ማንችስተር ዩናይትድ ተሸንፏል።
የመርሲሳይዱ ሊቨርፑል በስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በክሪስታል ፓላስ በሊጉ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
ቼልሲ እና ሊቨርፑል በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ200ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 199 ጨዋታዎች ሊቨርፑል 87 ጊዜ ሲያሸንፍ ቼልሲ 66 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 46 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በሊግ የውድድር ፎርማት ባደረጓቸው 166 ጨዋታዎች ሊቨርፑል 72 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ቼልሲ 52 ጊዜ አሸንፏል። 40 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ባለፉት 10 የሊግ ጨዋታዎች በነበራቸው ግንኙነት ሊቨርፑል ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ቼልሲ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በጉዳት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ቼልሲ ቁልፍ ተጫዋቹን ኮል ፓልመር እና ሊያም ዴላፕን ጨምሮ ስምንት ተጫዋቾችን በነገው ጨዋታ አያሳልፍም።
ተከላካዩ ትሬቮህ ቻሎባህ በቅጣት የማይሰለፍ ሲሆን በቀይ ካርድ ምክንያት የብራይተኑ ጨዋታ ያመለጠው ግብ ጠባቂው ሮበርት ሳንቼዝ በዛሬው ጨዋታ ይሰለፋል።
በሊቨርፑል በኩል የግብ ዘቡ አሊሰን ቤከር ከጋላታሳራይ ጋር በነበረው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ባጋጠመው ጉዳት ለስድስት ሳምንታት ከሜዳ ይርቃል። የ25 ዓመቱ ጂዮርጂ ማማርዳሽቪሊ አሊሰንን ተክቶ በጨዋታው ላይ ይሰለፋል።
በተመሳሳይ በጨዋታው ጉዳት አጋጥሞት የወጣው ሁጎ ኢኪቲኬ ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን በጨዋታው ላይ ሊሰለፍ ይችላል እየተባለ ነው።
የ46 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ከዌስትሃም ዩናይትድ እና ማንችስተር ዩናይትድ ከሰንደርላንድ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ላይ ሊድስ ዩናይትድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ይጫወታሉ።