ፊንላንድ ኢትዮጵያ በከባቢ አየር ጥበቃ እያከናወነች ላለው ስራ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ፊንላንድ ኢትዮጵያ በከባቢ አየር ጥበቃ እያከናወነች ላለው ስራ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች
አዲስ አበባ፤መስከረም 23/2018 (ኢዜአ)፦ ፊንላንድ ኢትዮጵያ በከባቢ አየር ጥበቃ እና ንጽህናው የተጠበቀ ስፍራን ለማስፋት የምታከናውነውን ስራ በተጠናከረ መልኩ መደገፏን እንደምትቀጥል አስታወቀች።
በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ፊንላንድ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ኢኒሼቲቮች በአፍሪካ ማዕቀፎቿ እየደገፈች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
የሀገራቸው የፊንላንድ የንግድ ተቋማት ከኢትዮጵያ የቢዝነስ ስራዎች በተለይም አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እና ጀማሪ የስራ ፈጣሪዎች ጋር እንዲሻረኩ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።
ፊንላንድ ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ በተለይም ምርቶችን እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል የኢኮኖሚ ጠቀሜታን ማግኘት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትፈልግም ነው የገለጹት።
ምርቶችን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ኢኒሼቲቮች ለስራ እድል ፈጠራ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ወጣት የማህብረሰብ ክፍል እና መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ተዳምሮ ለአዳዲስ የስራ እድሎች መፈጠር በር ይከፍታል ነው ያሉት።
አምባሳደር ሲኒካ ፊንላንድ ምርቶችን በስፋት መልሶ የመጠቀም ባህል እንዳላት ገልጸው፥ ይህ ልምምድ ዳግም ጥቅም ላይ ከማዋል ባለፈ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ እድገት አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በአንድ ዘርፍ የሚወገድ ምርት ለሌላ ዘርፍ ጥሬ ግብአት ሊሆን ይችላል ያሉት አምባሳደሯ በኢትዮጵያም መንግስት፣ ኢንዱስትሪዎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጋራ ከሰሩ በዘርፉ አዳዲስ የኢንዱስትሪ አይነቶች መፍጠር እንደሚቻል አስረድተዋል።
አምባሳደሯ ቆሻሻን መልሶ መጠቀም በርካታ የከባቢ አየር ትሩፋቶች እንዳሉት ጠቅሰው በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ያሉ ኢኒሼቲቮች የኢትዮጵያን ወንዞች ከብክለት ከመከላከል በተጓዳኝ የኢኮኖሚ እድገትን እንደሚያሳልጡ ተናግረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ እየተተከሉ ያሉ በርካታ ችግኞች ብክለት እና ቆሻሻን በማስወገድ እንዲሁም የምርቶችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም የኢኮኖሚ ስርዓቱን በመደገፍ ረገድ ጠንካራ አቅም እንደሆነ ነው አምባሳደሯ የገለጹት።
መጠነ ሰፊ የዛፍ ተከላን ከምርት መልሶ በመጠቀምና የኢኮኖሚ ኢኒሼቲቮች ጋር ትስስር በመፍጠር የኢትዮጵያን ከባቢ አየር ንጹህ እና ውብ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።
ከዚህ አኳያም ፊንላንድ ኢትዮጵያ በከባቢ አየር ጥበቃ እና ንጽህናው የተጠበቀ ስፍራን ለማስፋት እያከናወነች ያለውን ስራ በተጠናከረ መልኩ መደገፏ እና ልምዷን ማጋራት እንደምትቀጥል አምባሳደሯ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1959 በይፋ መመስረታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ በ1967 የሁለትዮሽ የልማት ትብብር በመፈራረም በተለያዩ መስኮች እየሰሩ ይገኛሉ።
ሀገራቱ በከባቢ አየር ማዕቀፍ በተለይም ምርቶችን ዳግም ጥቅም ላይ በማዋል የኢኮኖሚ አማራጮች፣ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ እንዲሁም የውሃ አስተዳደር ላይ ለረጅም ጊዜ የቆየ ትብብር አላቸው።