ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሺፕ ኢንቨስትመንት ባንክ ሊቋቋም ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢንተርፕርነርሺፕ ኢንቨስትመንት ባንክ ሊቋቋም ነው፡፡

ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢንተርፕርነርሺፕ ኢንቨስትመንት ባንክ ማቋቋም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈርሟል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ስምምነቱን ፈርመውታል፡፡

የኢንተርፕርነርሺፕ ኢንቨስትመንት ባንኩ መቋቋም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢንተርፕራይዞች አቅም መጎልበት ወሳኝ ሚና ይኖረዋልም ተብሏል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢንቨስትመንት ባንኩ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበት ነው።

መንግስት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያወጣቸውን ፖሊሲዎች ወደ ተግባር እየቀየረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢንተርፕርነርሺፕ ኢንቨስትመንት ባንክ የወጣቶችን ጥያቄ መመለስና የፈጠራ አቅማቸውን ማጎልበት ያስችላልም ብለዋል፡፡

ባንኩ በ20 ሚሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል የሚቋቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ 10 ሚሊዮን ዶላሩ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በድጋፍ የተገኘ ሲሆን ቀሪው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እንደሚሸፈን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግስት የወጣቶች የሥራ ፈጣሪነት አቅም እንዲጎለብት የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ነድፎ ተግባራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ባንኩ ወጣቶች ስታርታፖችን እና የሥራ ፈጠራ ሀሳባቸውን በቀላሉ ወደ ተግባር መቀየር የሚችሉበትን የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

ስታርታፖቹ የሚያቀርቡትን ሀሳብ አዋጭነት በመገምገም የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ ወጣቶች ለባንኩ የሚያስይዙት የፈጠራ ሀሳባቸውን ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ወጣቶች በካፒታል ገበያ ላይ በብዛት የሚሳተፉበት ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።

ኢንቨስትመንት ባንኩ ራሱን ችሎ የሚቋቋም ሲሆን፤ በቀጣይም የተለያዩ ተቋማትን በማሳተፍ የኢንቨስትመንት አቅሙን የበለጠ ያጠናክራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም