ቀጥታ፡

የጋራ እሴቶችን በማጠናከር መንግስት የጀመራቸው ዘመን ተሻጋሪ የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ የበኩላችንን እንወጣለን-የኢሬቻ ፎረም ተሳታፊዎች

ቢሾፍቱ ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፡- የጋራ እሴቶችን በማጠናከር መንግስት የጀመራቸው ዘመን ተሻጋሪ የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ የኢሬቻ ፎረም ተሳታፊዎች ተናገሩ።

7ኛው የኢሬቻ ፎረም የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎችን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ተካሄዷል።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የፎረሙ ተሳታፊዎች እንዳሉት የገዳ ስርዓት አንዱ አካል የሆነው ኢሬቻ አብሮነት እና አንድነት የሚጠናከርበት ትልቅ አገራዊ እሴት ነው።

ኢሬቻን ጨምሮ ሌሎች ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴቶችን በማጠናከር በመንግስት የተጀመሩ ለትውልድ የሚተርፉ የልማት ውጥኖች እንዲሳኩ ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።

ከተሳተፊዎቹ መካከል ፍሮምሳ ዴሶ እንደሚለው ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ በዓል ሳይሆን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት የጋራ እሴት ነው።


 

የኢሬቻን በጎ እሴት ለአብሮነት ማጠናከሪያ በማዋል የተጀመሩ የልማት ስራዎች እንዲሳኩ ከመንግስት ጎን በመሆን የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ የልማት ፕሮጀክቶችን እያጠናቀቀ ሌሎችን እየጀመረ መሆኑ ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።

ሌላው የፎረሙ ተሳታፊ ካሱ ማሞ፣ አሁን ያለው መንግስት የህዝቡ ባህል እና እሴት እንዲጠናከር እና አብሮነት እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑ አንዱ ማሳያ እያደገ የመጣው የኢሬቻ በዓል ነው ብለዋል።


 

መንግስት ከዚህ ቀደም ለማሰብ እንኳን የሚከብዱ ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ስራዎችን እየተገበረ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸው የተጀመሩ የልማት ስራዎች ለስኬት እንዲበቁ የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በለውጡ መንግስት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ትልቅ መነሳሳትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የፎረሙ ተሳታፊ ጉታማ ቲቤሳ ናቸው።


 

ባለፉት ዓመታት መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች በየአካባቢው ትልቅ ለውጥ እየታየ መሆኑን ጠቅሶ በቢሾፍቱ ከተማ የተመለከቱትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የመንግስት የልማት እቅዶች እንዲሳኩ በሚችሉት አቅም ሁሉ ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ገልጸዋል።

መሰረት አሰፋም እንዲሁ ''መንግስት ያለ ህዝብ ተሳትፎ ውጤት ስለማያመጣ ከእኔ ጀምሮ የተሰሩትን ፕሮጀክቶች በመጠበቅ የቀሩትን እየጠየቁ ከመንግስት ጎን መሆን ይገባል'' ብለዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ስራዎች ለማመን የሚከብዱ ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ የታቀዱ የልማት ውጥኖችም ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም