ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩ እድሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ  ምርታማነት የላቀ ሚና አላቸው - ሚኒስትር መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፡-በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩ እድሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ  ምርታማነት የላቀ ሚና እንዳላቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለፁ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የማምረት አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ከግሉ ዘርፍ ተቋማትና ማህበራት ጋር ምክክር አካሒዷል።


 

በዚሁ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ መንግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ እድል ፈጥሯል።

የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለመጨመርና የአምራች ዘርፉን እድገት ለማሳደግ የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር የሚያጠናክሩ የማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና አካታች የኢንዱስትሪ ልማት ተግባራዊ በመደረጉ ለዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪው የገበያ ድርሻ 30 በመቶ እንደነበር አስታውሰው፤ በተከናወኑ የለውጥ ተግባራት ምጣኔውን ወደ 45 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል።

በዘርፉ የሚፈጠረውን የስራ እድል  በእጥፍ በመጨመር ያለውን ሚና ማጉላት ተችሏል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በትላንትናው እለት የተመረቀውና የኢነርጂ ምንጭ የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ለዘርፉ ማንሰራራት ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን አስታውቀዋል።

እነዚህ ተግባራት የአምራች ኢንዱስትሪው ምርታማነት እንዲጨምርና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ዘላቂነት ለማረጋጥ ያግዛሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጀመሩ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ተጨማሪ እድልና አቅም ስለመሆኑም አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩ እድሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት መጨመር የላቀ ሚና እንዳላቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ምክክሩ አምራች ኢንዱስትሪው እይታውን በማስፋት አቅሙን አሟጦ እንዲጠቀምና ቅንጅታዊ አሰራሩን እንዲያጠናክር የሚያግዝ ነው ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ሰለሞን ሙሉጌታ እንደተናገሩት፤ ምክክሩ አምራቾች አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ምክረ-ሃሳብ የተሰጠበት ነው።


 

በተጨማሪም አገሪቷ ያላትን እምቅ ሃብት አሟጦ በመጠቀም የዘርፉን ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚቻልበት አማራጭ የተመላከተበት ስለመሆኑም አክለዋል።

የማሽነሪ አምራቾች ማህበር ሊቀመንበር አክሊሉ አባተ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ምክክሩ መንግስት በዘርፉ ተግባራዊ እያደረገ ያለውን አሰራር ለማስገንዘብና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያገዘ ነው።


 

በተጨማሪም በመንግስትና በአምራቹ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ የስራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እድል መፍጠሩን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም