ቀጥታ፡

የህክምና አገልግሎትና ስልጠናን በማጠናከር የጤና ስርዓቱን ለማዘመን ከአጋር አካላት ጋር የሚደረገው ትብብር ይጠናከራል-የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፡-የህክምና አገልግሎትና ስልጠናን በማጠናከር የጤና ስርዓቱን ለማዘመን ከአጋር አካላት ጋር የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ገለፁ።

የአውሮፓ ህብረት ከጣሊያንና ስፔን መንግስታት ጋር በመተባበር 146 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ለስድስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ድጋፍ አድርገዋል።


 

ድጋፉን የአውሮፓ ህብረት ሚስዮን ምክትል መሪ አኒያስካ ካምፒኒስኪ፣ በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ግዮርሞ ሎቬዝ ማህሊላን በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ ሚስዮን ምክትል መሪ ሉካ ካርፔንቴሪ ለዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ኃላፊዎች አስረክበዋል።

በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ እንዳሉት የአውሮፓ ህብረት ከስፔንና ጣሊያን የልማት አጋሮች ጋር በመሆን ባለፉት ሰባት አመታት ለጤና ዘርፍ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህም በስድስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የስፔሻሊቲ ህክምና ትምህርት እና የህክምና ስርዓቱን ለማጠናከር የሚያግዝ 146 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ድጋፉ የተደረገው ለመቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ሀረማያ፣ ጅማና አዳማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች መሆኑንም ገልጸዋል።


 

መሳሪያዎቹ ለህፃናት፣ አጥንት፣ ድንገተኛ፣ ማህፀንና ፅንስ እንዲሁም ሰመመን ህክምና የሚጠቅሙ መሆናቸውን ገልፀው፤ የህክምና አገልግሎት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቁመው፤ በዚህ ሂደት አጋር አካላት ድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልፀዋል።

አጋር አካላት የጤና አገልግሎትን ለማዘመን የሚያስችል የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍና ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት ሚስዮን ምክትል መሪ አኒያስካ ካምፒኒስኪ በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ ከአውሮፓ ህብረት አባል አገራቱ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሚተገብረው ኢኒሼቲቭ አካል መሆኑን ገልፀዋል።


 

የአውሮፓ ህብረት የህክምና ማህበራት ከዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነና በቀጣይም ኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጥረት ለማገዝ የምናደርገው ድጋፍ ይጠናከራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ግዮርሞ ሎቬዝ ማህሊላን በጤናው ዘርፍ የህክምናና የባለሙያዎች ስልጠና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ የጣሊያን ኤምባሲ ሚስዮን ምክትል መሪ ሉካ ካርፔንቴሪ እያደረጉ ያሉት ትብብር በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ያለው አበረታች ውጤት አካል መሆኑን ገልፀዋል።


 

ድጋፉን የተረከቡ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ኃላፊዎች በበኩላቸው የህክምና መሳሪያዎቹ የሚሰጡትን የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አህመድ ዘይኑዲን የተደረገላቸው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ የመማር ማስተማርና የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።


 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር በቃሉ ውብሸት ድጋፉ የሆስፒታሉን በተለይ የአጥንት፣ ኦፕሬሽንና ፅኑ ህክምና አገልግሎትን ለማሻሻል ይረዳል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም