ቀጥታ፡

ኢሬቻ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው ድንቅ እሴቷ ነው -የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፡-ኢሬቻ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው ድንቅ እሴቷ ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ባስተላለፈው የኢሬቻ በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ኢትዮጵያ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለዓለም ማበርከቷን ገልጿል፡፡ 

እሴታቸውን ጠብቀው ለዘመናት በሕዝብ እየተከበሩ የዘለቁ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላትንና ትውፊቶቻቸውን በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰው ልጆች ሁሉ ሀብት ተብለው እንዲመዘገቡም አድርጋለች ብሏል፡፡ 

ለምዝገባ በሂደት ላይ የሚገኙ በርካታ እሴቶች ባለቤትም ነች ሲል ነው የገለጸው፡፡

ኢሬቻ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር የይቅርታ እና የምስጋና በዓል መሆኑን የገለጸው አገልግሎቱ በዓሉ በዋናነት ክረምት በሰላም አልፎ ዐዲስ ዘመን መበሰሩን አስመልክቶ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት መሆኑን አመላክቷል፡፡

ምስጋናው ደግሞ ይቅርታን ያስቀድማል፤ የተጣላ ይቅር ተባብሎ በአንድ ቦታ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ነውና ያለው አገልግሎቱ ይህ ድንቅ የኢትዮጵያ እሴት የዓለም ሀብት እንዲኾን ኢትዮጵያ ለዘመናት ጠብቃዋለች፤ ትጠብቀዋለችም በማለት ገልጿል፡፡ 

የሚጠበቀው ደግሞ በዓሉን ትውፊቱን፣ እሴቱን፣ አሳታፊነቱን ጠብቆ በማክበር እና በማስተዋወቅ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ እና መላው ኢትዮጵያውያን የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ምስጋና የሚያቀርቡት በጋራ ድላቸው ያሳኩትን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የደስታ ስሜት እያጣጣሙ ነው ሲልም ገልጿል፡፡ 

በይቅርታ መሻገር፤ በጋራ ድል ማድረግ፤ በጋራ ማመስገን የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነውና፤ እንደ ኢሬቻ ያሉ የይቅርታ እና ምስጋና እሴቶች ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ጉልህ ድርሻ አላቸው በማለት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቱን አስተላልፏል፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም