በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲከናወን ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው - ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲከናወን ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው - ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ
ሐረር፤ መስከረም 23/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲከናወን የሀገርን ሰላምና ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ገለጹ።
የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ በሚገኘው በገርባሳ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠና ላይ ለሚገኙ የሰራዊቱ አባላት መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በሐረር ቤተ መንግስት ሁለገብ አዳራሽ በመገኘትም በየደረጃው ካሉ የሰራዊቱ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል መሐመድ በንግግራቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሰላም ከማስከበር ባለፈ በሌሎች አገሮችም ከፍተኛ ስምና ዝና ያለው ጠንካራ ሰራዊት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲከናወን የሀገርን ሰላምና ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች ጥምረት በመፍጠር ሀገር ለማፍረስ እየጣሩ መሆኑን ያነሱት ሌተናል ጄኔራል መሐመድ በሰራዊቱ ጀግንነትና ቁርጠኝነት በአስተማማኝ መልኩ እየተመከተ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሚሞክር አካል ካለ ሰራዊቱ የላቀ ዝግጁነትና የተሟላ የመፈፀም አቅም ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የከፍታ ጉዞ ለማሳካት የሰራዊቱን ባህርያትና እሴቶችን በመላበስ በአመራሩ የተሰጡ ግዳጆችን በድል መወጣት ይገባል ብለዋል።
የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ፤ በበኩላቸው የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት ላይ ስለመሆናቸው አንስተው ምንም አይነት መስተጓጎል እንዳይገጥም ለስኬታማነታቸው ሰራዊቱ ሌት ከቀን ስለመቆሙም አረጋግጠዋል።
በስልጠና ላይ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላትም ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።
በሐረር ቤተ መንግስት በተካሄደው የውይይት መድረክም የሰራዊቱ አባላትና ከፍተኛ መኮንኖች ተሳትፈዋል።