የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያን የናፍጣ እና የቤንዚን ፍላጎት ከ80 እስከ 90 በመቶ የመሸፈን አቅም አለው - ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያን የናፍጣ እና የቤንዚን ፍላጎት ከ80 እስከ 90 በመቶ የመሸፈን አቅም አለው - ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፦ የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን የናፍጣ እና የቤንዚን ፍላጎት ከ80 እስከ 90 በመቶ የመሸፈን አቅም እንዳለው የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በአመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ትናንት በይፋ በመመረቅ የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በማህፀኗ የያዘቻቸው የማዕድን ሀብቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በአይነትም በብዛትም ተከማችተው ይገኛሉ ብለዋል።
የኦጋዴን ሰርጥ ከብዙዎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል በተፈጥሮ ጋዝ እና በድፍድፍ ነዳጅ ከፍተኛ ክምትች ያለው እንደሆነ ከእ.አ.አ 1920ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ይህ ሀብት እንዳለና በተለይም ከእ.አ.አ 1940ዎቹ አንስቶ ጥልቅ ፍለጋዎችና ምርመራዎች በተለያዩ ኩባንያዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አውስተዋል።
እ.አ.አ. 1970ዎቹ የነዳጅ ጉድጓድ መቆፈር ተጀምሮ በርካታ ኩባንያዎች በተለያዩ የኦጋዴን አካባቢዎች የነዳጅ ቁፋሮዎችና ጥናቶች ሲያካሂዱ መቆየታቸውን ነው ያወሱት።
መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ተከትሎ ከጂሲኤል ኩባንያ ጋር በአዲስ መልኩ በመፈራረም የፍለጋ ጥናቱ ከተጀመረ ከ85 ዓመታት በኋላ የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮዎች ከተጀመረ ከ53 ዓመታት በኋላ ስራው መጀመሩን አመልክተዋል።
በአንድ ዓመት ከሁለት ወር ፈጣን ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኦጋዴን ጋዝ ልማትን በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ገበያ ማቀርብ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ይህም ፕሮጀክቶችን በቅጡ እቅዶ በከፍተኛ ትጋትና ክትትል ከባለሀብቶች ጋር በማልማት በአጭር ጊዜ ጀምሮ ማጠናቀቅ ባህል እየሆነ የመጣው ልምምድ ሌላው ማሳያ ነው ብለዋል።
ይህ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ወደ ውጭ ኤክስፖርት የሚደረግ እንደሆነም በማንሳት።
ኦጋዴን ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ስራዎች አስተማማኝ የሰላምና የልማት አካባቢ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው ፕሮጀክቶቹ የመልማት እና የመበልጸግ መሻትን የሚያሳኩ እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ ተስፋን የፈነጠቀ የልማት ጮራ ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ህያው ማሳያ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ በንግግራቸው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተፈጥሮ ጋዝን የሚያጣራ እና ወደ ፈሳሽነት የሚቀይር ፋብሪካን እውን አድርገናል ያሉት ሚኒስትሩ ይህም ፋብሪካዎችና ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት አዲስ የኃይል አማራጭ ነው ብለዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ከኦጋዴን ሰርጥ የሚወጣውን የተፈጥሮ ጋዝ እና ድፍድፍ ነዳጅ ለሚያቀነባብሩ አራት ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጉ የኃይል መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በማካተት እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቶቹ በተለመደው ባህል በፍጥነት እንደሚጠናቀቁም ነው የገለጹት።
ጎዴ ላይ የተጀመሩት በዓመት ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚያመርተው በአሁኑ ወቅት ፍጆታ ላይ የሚውለውን ሶስት እጥፍ ዩሪያ ማዳበሪያ የሚያቀነባብረው ዳንጎቴ ጎዴ የማዳባሪያ ፋብሪካ ስራ መጀሩንም አመልክተዋል።
ከካሉብ ወደ ጎዴ 108 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የነዳጅ ቱቦ በማካተት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው እና ከአምስት ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል።
ካሉብ ላይ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች እስከ ሶስት ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩ መሆናቸውንም እንዲሁ።
ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በከፍተኛ እድገት ላይ የሚገኘው በምግብ ራስን መቻል ወደ ማይቀለብስ ደረጃ የሚያደርሱና ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን ብልጽግና ትርጉም ወዳለው ደረጃ የሚያሸጋግሩ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና ያላቸው ናቸው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ማዕድን አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ እንዲሆን ከፍተኛ ጥናቶችና ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ የካሉብ ጋዝ ማቀነባበሪያ ፋብሪካና ግንባታቸው የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የጥናቶች እና ዝግጅቶቹ ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ማህጸነ ለምለሟ ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ከራሷ አልፋ ለዓለም የሚተርፉ እጅግ የበዙ እና ውድ ማዕድን ሀብቶች እንዷላት ጠቅሰው ኦጋዴን ሰርጥ ላይ የተጀመረውን የማዕድን ልማት በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።