ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ካሏት ድንቅ ባህላዊ እሴቶች አንዱ የሆነው ኢሬቻ አብሮነትን የሚያጠናክር በዓል ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ካሏት ድንቅ ባህላዊ እሴቶች አንዱ የሆነው ኢሬቻ አብሮነትን የሚያጠናክር በዓል መሆኑን የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ ገለጹ።

7ኛው የኢሬቻ ፎረም "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በቢሾፍቱ ከተማ ሆረ ሀርሴዴ አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በፎረሙ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር)፣ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረህማን፣ ሚኒስትሮች፣ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ፤ የኢሬቻ በዓል ኢትዮጵያ ካሏት ድንቅ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱና አብሮነትን የሚጠናከርበት ነው ብለዋል።

ኢሬቻ ሰላምና ምስጋና፣ እርቅና ይቅርታ፣ አብሮነትና ወንድማማችነት የሚንጸባረቅበት ውብ ባህላዊ እሴቶችን በውስጡ የያዘ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት አንዱ መገለጫ መሆኑን ገልፀው የኦሮሞ ህዝብ ለዓለም ያበረከተው የኢትዮጵያ ድንቅ ባህላዊ ሀብት ነው ብለዋል።

ቢሮው የክልሉን ባህላዊ ሀብቶች በላቀ ደረጃ ለማስተዋወቅና ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለአብነትም ከገዳ ስርዓት የተቀዱ የባህል ፍርድ ቤት፣ የመረዳዳት እሴት መገለጫ የሆነው የቡሳ ጎኖፋ የመሳሰሉ ባህላዊ እሴቶችን የመንከባከብና የማጠናከር ሥራ በመከናወን ላይ ነው ብለዋል።

ኢሬቻን የቱሪዝም ዋነኛ መዳረሻ በማድረግ ለሀገር የገቢ ምንጭ ማደግ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ቀጣይነት ያለው ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው፥ ከተማዋ የባህል እና የቱሪዝም ማዕከል መሆኗን ጠቁመው ኢሬቻ የቢሾፍቱ መድመቂያ ሆኗል ብለዋል።

የቱሪዝም ማዕከልነቷን ለማጠናከርም የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ነገ መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ እንዲሁም መስከረም 25 ቀን በቢሾፍቱ ሆራ ሀርሰዲ "ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት" በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም