በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩ እድሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የላቀ ሚና አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩ እድሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የላቀ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፦ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩ እድሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት የላቀ ሚና እንዳላቸው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለፁ።
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የማምረት አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ከግሉ ዘርፍ ተቋማትና ማህበራት ጋር ምክክር እያካሔደ ይገኛል።
በዚሁ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ባስተላለፉት መልእክት መንግስት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ እድል ፈጥሯል።
የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለመጨመርና የአምራች ዘርፉን እድገት ለማሳደግ የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር የሚያጠናክሩ የማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና አካታች የኢንዱስትሪ ልማት ተግባራዊ በመደረጉ ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ እድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
የኢንዱስትሪው የገበያ ድርሻ 30 በመቶ እንደነበር አስታውሰው፤ በተከናወኑ የለውጥ ተግባራት ምጣኔውን ወደ 45 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል።
በዘርፉ የሚፈጠረውን የስራ እድል በእጥፍ በመጨመር ያለውን ሚና ማጉላት ተችሏል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በትላንትናው እለት የተመረቀውና የኢነርጂ ምንጭ የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ለዘርፉ ማንሰራራት ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን አስታውቀዋል።
እነዚህ ተግባራት የአምራች ኢንዱስትሪው ምርታማነት እንዲጨምርና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ዘላቂነት ለማረጋገጥ ያግዛሉ ብለዋል።
በተጨማሪም የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጀመሩ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ተጨማሪ እድልና አቅም ስለመሆኑም አንስተዋል።
በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈጠሩ እድሎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት መጨመር የላቀ ሚና እንዳላቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።