የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊነት ቀለም ጎልቶ የሚታይበት የጋራ እሴት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያዊነት ቀለም ጎልቶ የሚታይበት የጋራ እሴት ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፦ኢሬቻ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር የምንሰባሰብበት የኢትዮጵያዊነት ቀለም ጎልቶ የሚታይበት በዓል ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢሬቻ የምስጋና በዓል፣ ከክረምት ወቅት መለያየትና መራራቅ በኋላ ሰዎች በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃቸውን ፈጣሪ የሚያመሰግኑበት በዓል ነው።
ኢሬቻ ህዝቦች በጋራ የሚያከብሩትና በርካታ የዓለም ቱሪስቶች የሚታደሙበት በመሆኑ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና የኢትዮጵያ ድንቅ ባህል ጎልቶ የሚታይበት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢሬቻ ከክረምት ጨለማ ወደ ጸደይ ብርሃን መውጣትን ተከትሎ ምስጋና የሚቀርብበት እና ሁሉም በራሱ ቀለም ደምቆ የሚታይበት መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ደጀኔ ጎሹ ተናግረዋል።
ኢሬቻ አሁን ከኢትዮጵያም አልፎ የዓለም እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፤ ኢሬቻ እና ሌሎች ባህሎቻችንን ለባህል እድገትና የቱሪዝም ልማት መጠቀም አለብንም ብለዋል።
ወይዘሮ ምጽላል መስፍን በበኩላቸው፤ ኢሬቻ ለየት የሚያደርገው ለሴቶች እኩልነት የሚሰጥና በአከባበሩ ላይም ሴቶች ከፊት ለፊት የሚሄዱበት ለየት ያለ የኢትዮጵያ ኃብት ነው ብለዋል።
ይህም የገዳ ስርዓት ዲሞክራሲያዊነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢሬቻ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲቆይ ሁላችንም መጠበቅ አለብንም ሲሉም ጠቁመዋል።
ኢሬቻ ሁሉም በጋራ ሆኖ የሚያከብረውና የውጪ አገራት ቱሪስቶች የሚሳተፉበት ለአገር ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኝ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
ወይዘሮ አይናለም በቀለ በበኩላቸው ኢሬቻ ሁሉም በጋራ የሚያከብረውና በርካታ ውብ እሴቶች ያሉት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢሬቻ አብሮነትና መሰባሰብ የሚታይበት ወንድማማችናትና እህትማማችነት የሚጠናከርብት መሆኑንም አንስተዋል።