በመንግሥት ቁርጠኝነት ታሪካዊ ስኬት የሆኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በክልላችን እየተገነቡ ነው - የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
በመንግሥት ቁርጠኝነት ታሪካዊ ስኬት የሆኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በክልላችን እየተገነቡ ነው - የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 23/2018(ኢዜአ)፡- በፌደራል መንግሥት ቁርጠኝነት ታሪካዊ ስኬት የሆኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በሶማሌ ክልል እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ እና በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የሚገነባው የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በዚሁ ወቅትም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ባደረጉት ንግግር፤ በመንግሥት ቁርጠኝነት የተመረቀው ብሎም የሚገነቡት ትላልቅ ፕሮጀክቶች የክልላችን ብሎም የሀገራችን ታሪካዊ ስኬቶች ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ፋይዳቸው ዘርፈ-ብዙ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ መሆኗን ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል እንደክልል ብሎም እንደሀገር በቁርጠኝነት እየተከናወኑ ያሉትን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥና ከድህነት የመላቀቅ ጉዞ ያፋጥናሉ ነው ያሉት።
በዚህም የሶማሌ ክልልን ብሎም የኢትዮጵያን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ሂደት እነዚህ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል በንግግራቸው።
ትናንት አጀንዳችን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ማስገባት ነበር፤ አሁን ደግሞ ትኩረታችን የምግብ ሉዓላዊነትንና ዘርፈ-ብዙ የልማት ተደራሽነትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።
ይህን ከሀገር አልፎ ለአህጉር የሚተርፍ ሐሳብ በማመንጨትና በመተግበር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እያበረከቱት ላለው ድንቅ ተግባር ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በዚሁ መሠረት ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የፌደራል መንግሥት ለሶማሌ ክልል ትኩረት መስጠቱንና በዚህም በተለያዩ ዘርፎች አስደናቂ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
ለአብነትም ከተመዘገቡ ተጫባጭ ለውጦች መካከል፤ በግብርና፣ በመንገድ መሠረተ-ልማት፣ በንጹህ መጠጥ ውኃ እንዲሁም በሆስፒታል ማስፋፋት የተከናወኑትን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ትናንት የተመረቀውና በቀጣይ እንዲገነቡ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ደግሞ የፌደራል መንግሥት የሶማሌ ክልል በየዘርፉ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ታሪካዊ ስኬት ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቶቹ ፋይዳ በርካታ መሆኑን ጠቁመውም፤ ለአብነትም የሀገራችንን የኢንቨስትመንት ተመራጭነት በማሳየት፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለዕውቀት ሽግግር፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና በሌሎችም ጉዳዮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አብራርተዋል።
የዳንጎቴ ግሩፕ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሊኮ ዳንጎቴ እንዲሁም የቻይናው ጂሲኤል ኩባንያ ሊቀ-መንበር ዡ ጎንግሻንን አመሥግነው፤ በክልሉ በሚኖራቸው ልማታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ሁሉ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።